ቁርአን ስለ ፍርድ ቀን

M.J Fisher, M.Div.

ቅንብር በአዘጋጁ

ማብራሪያና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ንፅፅር

መጽሐፍ ቅዱስም ቁርአንም የመጨረሻውን ፍርድ ቀን በተመለከተ ያስተምራሉ፡፡ በቁርአን ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ የመጨረሻው ቀን አሰቃቂ ሁኔታዎች መሐመድ ከመወለዱ ብዙ መቶ ዓመታት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገሩትን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም በመጽሐፍ ቅዱስ መልእክትና በቁርአን መካከል እጅግ ብዙ የሚሆኑ ልዩነቶች አሉ፡፡ ይህን የመጨረሻውን ፍርድ በተመለከተ በቁርአን ውስጥ ያሉት ሠላሳ አምስት ጥቅሶች በአጭሩ ተሰብስበው በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ከመጨረሻው ፍርድ አስቀድሞ ምን እንደሚሆን ግልፅ የሆኑ ትንቢቶችን ይናገራል፡፡ ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ እንደሚዳረስ ማቴዎስ 24.14፡፡ የሐሰተኛውን ነቢይ ስራ ራዕይ 13፡፡ የመጨረሻው የዓለም ጦርነት በትክክል የት ቦታ እንደሚሆን ራዕይ 16.16፡፡ እነዚህ እጅግ በጣም ብዙ ከሆኑት ትንቢቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በቁርአን ውስጥ እንደዚህ ግልጥና ውስን የሆኑ ትንቢቶች በፍፁም አይገኙም ነገር ግን ከዚህም እጅግ በጣም ብዙ አስገራሚ የሆኑ ልዩነቶች አሉ፡፡

ቁርአን የመጽሐፍ ቅዱስን ማዕከላዊ መልእክት ማለትም የጌታ የኢየሱስን በድል ዳግም የመመለስን ነገር አይጠቅስም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ዙፋን ማዕከል ላይ እንደ ንጉስም እንደ አዳኝም እንደሚቀመጥ ይናገራል ማቴዎስ 25፤ እና ራዕይ 7.16-17፡፡ የፍርድ ቀንን በተመለከተ አንድ የቁርአን አንቀፅ ኢየሱስን የሚጠቅሰውና የሚያቀርበው በአላህ ፊት ፈተና እንደሚቀርብለት አድርጎ ነው፡፡ አላህ ኢየሱስን የሚጠይቀው እሱና እናቱ ማርያም ከአላህ ጎን ሁለት አማልክት ናቸው ብሎ ተናግሮ እንደሆነ እና እንዳልሆነ ነው ለዚህም ኢየሱስ የሚመልሰው መልስ እንዲህ ዓይነትን ነገር በጭራሽ እንዳላደረገው ነው 5.115-117፡፡

ቁርአን የሚናገረው ኢየሱስ በጌትነቱ ያመኑትን እንደሚያድን ሆኖ አይደለም፡፡ በእርግጥ ደኅንነት የሚባል ነገር በእስልምና ውስጥ የለም (አይታወቅም)፡፡ አንድ ሰው በእስልምና የዘላለም ገነት ውስጥ መግባት ካለበት ለእስልምና ተዋግቶ የሞተ መሆን አለበት ወይንም ደግሞ በሚከተሉት በአራት ነገሮች የተረጋገጠለት መሆን አለበት፤ ሀ. አላህ በእስልምና እንዲያምን ምሪትን የሰጠው፣ ለ. መልካም ስራዎቹ ክብደት ያላቸው፣ ሐ. ሃይማኖታዊ ተግባራትን እንደሚገባ የጠበቀ እና መ. አላህ በእሱ ላይ ምህረት ያደረገለት ሰው መሆን አለበት፡፡

ስለዚህም ይህንን በተመለከተ ቁርዓን የሚከተሉትን ነገሮች ይናገራል፡

ኢየሱስ ይጠየቃል፡- በፍርድ ቀን ከሌሎች ሐዋርያት ጋር ያለውን ኢየሱስን አላህ ይጠይቀዋል፤ ኢየሱስ ለሰዎች ልጆች እሱንና እናቱን እንደ ሁለት አማልክት ከአላህ ጎን እንዲያመልኳቸው ተናግሮ እንደሆነ ይጠየቃል እሱም በጣም አጥብቆ ይክዳል 5.115-117፡፡

ፀሐይ፡- በፍርድ ቀን ፀሐይ ትጠቀለላለች 81.1፡፡

ፀሐይና ጨረቃ ይጋጫሉ፤ ፀሐይና ጨረቃም አንድ ላይ ይሰበሰባሉ 75.9፡፡

ከዋክብት፡- ከዋክብት ይረግፋሉ 81.2፡፡

ተራራዎች፡- ተራራዎች ይነዳሉ 81.3፡፡

ሴት ልጆች፡- በሕይወቷ የተቀበረች ሴት ልጅ (ሴቶች በመሆናቸው) ተነስተው ይህ ለምን እንደተደረገባቸው ይጠየቃሉ 81.8-9፡፡

ሰማይ፡- ሰማይም ለሁለት ይሰነጠቃል 55.37፡፡

ትንሳኤ፡- በዚያን ቀን የሞቱት ከመቃብሮቻቸው ውስጥ ይወጣሉ ከዚያም ስራዎቻቸው ይጋለጣል 100.9-10፡፡

መሬት፡- ምድርም በተደጋጋሚ ትሰባበራለች 89.21፡፡

መጽሐፍት፡ እያንዳንዱ ሰው የእምነቱ መጽሐፍና ስራው ይሰጠዋል፡፡ ሰውየው መጽሐፉን በቀኝ እጁ የሚቀበል ከሆነ ፍርዱ ይቀልለታል፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ የተሰጣቸው ከጀርባቸው በኩል ከሆነ በሲዖል ውስጥ ይቃጠላሉ 84.7-12፡፡

ወደ ሰማይ መሰላል፡- በፍርድ ቀን መናፍስትና መላእክት በአንድ ቀን ወደ ሰማይ በመሰላል ይወጣሉ 70.4፡፡

ሃምሳ ዓመታት፡- የፍርድ ቀን በአንድ ቀን ውስጥ ይሆናል ያም የሃምሳ ሺ ዓመታት እኩል ነው የሚሆነው 70.4፡፡

በቶሎ ይሆናል፡- የማያምኑት የፍርድ ቀን በቶሎ የማይሆን ይመስላቸዋል ሙስሊሞች የሚያምኑት ግን በቶሎ እንደሚሆን ነው 70.6-7፡፡

ምንም መዳን የለም፡- ከፍርድ ቀን ታላቅ ስቃይ እራሱን ለማዳን ኃጢአተኛው ልጆቹን፣ ሚስቱን፣ ዘመዶቹን እና በዓለም ላይ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ለመሰዋት ቢችል ደስ ይለዋል፡፡ የሲዖልም ነበልባል ከኃጢአተኛው እራስ ላይ ፀጉርን ይነቅላል ምክንያቱም ባለማመኑና ሃብትን በማከማቸቱ ነው 70.10-18፡፡

ዙፋን፡- በፍርድ ቀን ሰማይ ይደክምና ይሰነጠቃል፡፡ የተሰነጠቀውም ሰማይ የአላህን ዙፋን በጭንቅላቶቻቸው የተሸከሙትን ስምንት መላእክትን እንዲታዩ ያጋልጣቸዋል 69.15-17፡፡

ሚዛን፡- በትንሳኤ ቀን የእያንዳንዱ ሰው ስራ በሚዛን ላይ ይመዘናል፡፡ እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት የሆነችው ስራ እንኳን ሳይቀር ትመዘናለች 21.47፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

የመጨረሻውን የፍርድ ቀን በተመለከተ እስልምናም ክርስትናም የሚናገሩት በጣም በጥቂቱ ይመሳሰል እንጂ ከዚህ በላይ እንደተገለፀው ጉልህ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ በፍርድ ቀን ስለሚሆነው ነገር ማወቅና ከፍርድ ቀን መዳንን ማወቅ የተለያዩም ነገሮች ናቸው፡፡ ስለ ፍርድ ቀን አውቀን ከፍርድ ቀን መዳን እንዴት እንደሚቻል ካላወቅን ግን እውቀታችን ሁሉ በእውነት ምንም ጥቅም አይኖረውም፡፡ ከላይ በመግቢያው ላይ እንዳየነው እስልምና ከፍርድ ቀን ስለመዳን ምንም የሚሰጠው ዋስትናም ሆነ ግልፅና ትክክለኛ መንገድ የለም፡፡

የፍርድ ቀን ዘላለምን የት ልናሳልፍ እንደምንችል የሚወስን ቀን ነው፡፡ ስለሆነም ይህንን በ ትክክል ማወቅ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አንባቢ ሆይ ስለዚህ ነገር ልታስብ እንደሚገባህ በእግዚአብሔር ፍቅር ልናሳስብህ እንፈልጋለን፡፡ የመጨረሻውን ቀን ፍርድ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት አስገራሚ ተስፋዎች አንዱን ከዚህ በታች እንድታነበውና እንድታስብበት እንጋብዝሃለን፡- ‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።› ዮሐንስ 3.16-18፡፡ ይህ በጣም ግልጥ ተስፋ ነው፡፡ ኃጢአቱን ተናዞ በክርስቶስ የሚያምነው ሰው ከፍርድ ነፃ የሚሆነውና የእውነተኛ ደስታን ሕይወት የሚያገኘው ካመነበት ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ እዚህ በምድር እያለ ያውቀዋል፣ ትልቅ ልዩነት አይደለምን ነው እንጂ! ስለዚህ ወደ ጌታ ኢየሱስ አሁኑኑ ናና የኃጢአትህን ይቅርታ ጠይቀው ከዘላለምም ፍርድ ነፃ ትሆናለህ የምድራዊ ሕይወትህም ከባዶነትና ከተስፋ መቁረጥ ነፃ ይወጣል፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ይርዳህ አሜን፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: Judgment Day, Chapter 8 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ