የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች
በREV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
ምዕራፍ አንድ:- መግቢያ
ዲሞክሪተስ የተባለው ጥንታዊ የግሪክ ፈላስፋ ‹ምንም ነገር ከምንም ነገር አይወጣም› በማለት በተናገረው የፍልስፍና አስተያየት ውስጥ ብዙ እውነታ አለበት፡፡ የመሐመድ ሃይማኖት ተብሎ በተከታዮቹ የሚጠራው እስልምናም ከዚህ የፈላስፋው አባባል በፍፁም የተለየ አይደለም፡፡ ያም ሃይማኖት በሰው ልጅ ታሪክ ለመልካም ወይንም ለመጥፎ የተጫወተው ሚናና አሁንም በብዙ ምስራቃዊ አገሮች የሚያሳድረው ከፍተኛ ተፅዕኖ፤ ከሃይማኖት፤ ከታሪክ ወይንም ከፍልስፍናም አንፃር እንኳን፤ ምንጩን ለመመርመር ያነሳሳል፡፡ ይህም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አንዱንና በጣም ጠቃሚ የሆነውን የታሪክ እንቅስቃሴ ምንነት መርምሮ ለማወቅ ከመጓጓት የተነሳ ነው፡፡ ስፕሬንገር እና ዌል በጀርመን እንዲሁም ሰር ሙር በእንግሊዝ ያደረጉት ጥረት የመሐመድን ሕይወትና ባህርይ እንዲሁም ስለመሐመድ ዓለም ጭምር ለማወቅ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ እንድናውቅ አስችሎናል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ነገሮች በተመለከተ እዚህ ላይ መጥቀስ አስፈላጊያችን አይደለም፡፡ መሐመዳውያን ሃይማኖታቸውን በቀጥታ ያገኙት ከመሐመድ እንደሆነ የመናገራቸው ነገር በአጠቃላይ የጋራ ግንዛቤ ነው፡፡ እነሱም መሐመድን የመጨረሻውና ታላቁ ነቢይ እንደነበረ፤ እምነታቸውም የተመሠረተው የመለኮትን መገለጥ የያዘ ነው በሚሉት በቁርአን ላይ እንደሆነ፤ ቁርአንም መሐመድ ለሰዎች ሊያስተላልፈው እንደተሰጠው ይናገራሉ፡፡
በዚህም ላይ ትልቅ ጠቀሜታን የሚያያይዙት ስልጣን ባላቸው ሐዲቶች ላይ ነው፡፡ ሐዲቶች በቃል ከነቢያቸው የተላለፉና እጅግ ረጅም የሆኑ የተከታዮቹ ዘገባ ሲሆኑ፤ እጅግ በጣም ቆይቶም በጽሑፍ እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡ እነዚህም ሁለቱ ማለትም፣ ቁርአንና ልማድ (ሐዲት) አብረው ሲወሰዱ የእስልምናን መሠረት ይሰጣሉ፡፡ ትልቅ ጠቀሜታም የተሰጠው ለጥንት የቁርአን ተንታኞች ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጥንት ሕግ አውጪዎች እና የሕግ ዶክተሮች ለተደረገው ስራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ የእስልምናን እምነትና የልማድን ምንጭ በተመለከተ ባደረግነው በእኛ ምርምር ውስጥ በሙስሊሞች በእርግጥ የሚታመነው ምንድነው ለሚለው ጥያቄ የሚሰጡት ፍንጭ እስከሌለ ድረስ በኋላ ስለመጡት ስለነዚህ ነገሮች እኛ የሚኖረን ሐሳብ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ልማዶቹም እራሳቸው እንኳን በእኛ ጥያቄ ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚመጡት፤ ምክንያቱም የእነሱ ስልጣን ቢያንስ-ቢያንስ፣ በዮሮፕያውያን አመለካከት በጣም እርግጠኛ አይደለምና፡፡
የመሐመዳውያን ልዩ ልዩ ቡድኖችም እንኳን የተቀበሉት የተለያዩ የልማድ ስብስቦችን ነው፣ ሰብሳቢዎች የነበሩት እራሳቸውም እንኳን በብዙዎቹ ስብስቦች ትክለኛነት ላይ ጥርጥር ነበረባቸው፡፡ በአብዛኛው ክፍላቸው ውስጥ ልማዶች በመሐመድ ንግግርና ስራ ላይ የሚናገሩ ሲሆን፤ እኛ እነሱን የምንጠቅሰው በአንዳንድ ነጥብ ላይ የቁርአንን ትምህርት በሚያጎሉበት ወይንም በሚያብራሩበት ሁኔታ ላይ ብቻ ነው፡፡ ቁርአን በጣም ስውር እና አስቸጋሪ የሆኑ ክፍሎችን ይዟል ይህም ሊገለጥ የሚችለው ልማዶችን በመመልከት ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌም አምሳኛው ቁርአን ወይንም ምዕራፍ የተሰየመው ‹ካፍ› ተብሎ ነው፤ ማለትም በአንዱ የአረብኛ ፊደል ስም ተሰይሟል ማለት ነው፡፡ ልማድን ካላየን በስተቀር ይህ ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ለማወቅ አይቻልም፡፡ ሐዲት ወይንም ልማድ ካፍ ስለተባለው ተራራ የተሰጠ መሆኑን በመናገር የምዕራፉ ስም ምን ማለት እንደሆነ ሲገልጠው ካላየን በስተቀር ትርጉሙን ማወቅ አይቻልም፡፡ እንዲሁም እንደገና ‹የምሽት ጉዞ (የሌሊት ጉዞ)› ተብሎ በተሰየመው ምዕራፍ 17 ውስጥ በመጀመሪያው ቁጥር ላይ ‹በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ ያ ባሪያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙሪያውን ወደ ባረክነው ወደ ሩቅ መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስኼደው (ጌታ) ጥራት ይገባው ከታምራቶቻችን ልናሳየው (አስኼድነው) እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚው ተመልካቺው ነው፡፡› የሚለውን እናነባለን፡፡ የዚህንም ጥቅስ ትርጉም ለማወቅ ልማድን መጥቀስ ይኖርብናል፡፡ እኛም መማር ያለብን ‹የእስላም ዑላማዎች ስለተጠቀሰው ጉዞ በትክክል እንደሚያውቁ ነው ይህም በአጠቃላይ የሚወሰደው ‹የመሐመድ መውጣት (ማረግ) ተብሎ ነው›፡፡
በሙስሊሞች መመሪያዎችና ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች፤ ዶክትሪኖችን ወይንም ተግባራዊ ነገሮችን በተመለከተ በቁርአን ውስጥ በግልጥ ወይንም በስውር ትምህርት ላልተሰጠበት ወይንም በቁርአን ውስጥ እራሱ ባልተገኘ ነገር ላናተኩር በራሳችን ላይ መመሪያ ማስቀመጥ አለብን፡፡ ወይንም በሁሉም የመሐመዳውያን ክፍሎች በአጠቃላይ ተቀባይነትን ባገኙት በእነዚያ ልማዶች ላይ ባልተገኘ ነገር አናተኮርም፤ ይህም በሕንድ ያሉትን አዲስ-መሐመዳውያንን በከፊል ሳይጨምር ነው፡፡ ምክንያቱም እነሱ በሌሎች ዓለም ባሉት መሐመዳውያን እንደሙስሊም አይቆጠሩምና፡፡
እውነተኛና ስልጣን አላቸው በሚባሉት ልማዶች ላይ መጠነኛ የመለኮት መገለጥ አለባቸው የሚባል እውነታ (በሙስሊሞች ዘንድ) መኖሩን መጠቆም መልካም ቢሆንም፤ ነገር ግን የእነሱ ስልጣን ከቁርአን በጣም የተለየ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ እነሱ ከቁርአን በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም የተጠቆመው በሁለቱ መካከል ባለው የተለያየ ዓይነት የመገለጥ መንገድ ልዩነት ምክንያት ነው፡፡ ቁርአን የተወሰደው ‹የመቅራት መገለጥ› ተደርጎ ሲሆን ልማዶች ግን ‹ያልተቀሩ መገለጦች› ተብለው ነው፣ ምክንያቱም ቁርአንና እርሱ ብቻውን የራሱ የእግዚአብሔር ንግግር ነው ተብሎ ስለሚወሰድ ነው፡፡ ስለዚህም የተቀመጠው ሕግ (መስፈርት) ማንኛውም ልማድ ምንም ዓይነት በሚገባ የተረጋገጠ ቢሆንም ከቁርአን አንድ ጥቅስ ጋር ተቃርኖ ከተገኘ ተቀባይነትን አያገኝም፡፡ ይህ መመሪያ ወይንም ሕግ የመሐመዳውያንን እምነት በተመለከተ ለምናደርገው ማንኛውም ነገር ልናስተውለው የሚያስፈልግ በጣም ጠቃሚ መመሪያ ነው፡፡ ይህም፤ ሐቀኛው የትኛው ልማድ ነው? አጠራጣሪው የትኛው ነው? እንዲሁም ተቀባይነት ያለው የትኛው ነው? ወደሚል ውስብስብና ጥልፍልፍ ነገር ውስጥ እራሳችንን እንዳናስገባ፣ ወደእነዚህ ውስጥ መግባትም አስፈላጊ እንዳይደለ ያደርግልናል፡፡ ለእኛም ለአሁኑ ዓላማችን ልማዶች በጽሑፍ መልካቸው ከቁርአን በጣም ዘግይተው መምጣታቸውን መገንዘብ በቂ ነው፡፡
በሁሉም ቦታ በሚገኙት መሐመዳውያን ዘንድ ቁርአን ተቀባይነት ያለው በመሆኑ እኛ ሙሉ የሆነና ብቃት ያለው መረጃ አለን ማለት ነው፡፡ የቁርአን አንዳንዶቹ ምዕራፎች በማንኛውም ነገር ላይ ተጽፈው የነበሩ ሲሆን፤ ወደ አንዳንዶቹ የመሐመድ ገልባጭ ጸሐፊዎች የመጡት በእጅ ነበር፡፡ የተነገረንም ነገር ከእነዚያ ጽሑፎች ውስጥ ብዙዎቹ እንደነበሩ ነው፣ እነሱም በእሱ እንደተቀሩ ወዲያውኑ የተደረጉ ነበር፡፡ በመሐመድ ጊዜ የመጻፍ እውቀት በመካዎች መካከል ያልተለመደ አልነበረም ምክንያቱም ከመካዎቹ አንዳንዶቹ ወደ መዲና በምርኮ ተወስደው በነበረበት ጊዜ ነፃነታቸውን ያገኙት የመዲናን ሰዎች ስነ ጥበብን በማስተማር እንደነበረ ተነግሮናልና፡፡ መገለጦቹ በአንድ ጊዜ ወይንም በብዙ ጊዜ ውስጥ ይጻፉ፣ እነርሱ ወዲያውኑ ለማስታዎስ በጣም ይተጉ ነበረ፤ እንዲሁም በማህበር አምልኮ ላይና በሌሎች ሁኔታዎችም ላይ ይቀሩ (ይታወሱ) ነበረ፡፡ በመሐመድ የሕይወት ዘመን ወቅት ስለ አንድ አንቀፅ ትክክለኛ ቃል አንድ የሆነ ጥርጥር ሲነሳ ብዙ ጊዜ ወደ እሱ ጥያቄ ይመጣ ነበር፡፡ ልማድ እንደጠቀሰው አንዳንድ ምዕራፎች እና ጥቅሶች በመሐመድ ሕይወት ጊዜ ተጽፈው በመሐመድ ሚስቶች ቤት ውስጥ ይቀመጡ እንደበረ ነው፡፡ እንዲያውም የተነገረን ነገር ከተቀመጡት መካከል አንዳንዶቹ ጥቅሶች እንደጠፉና በፍፁም እንዳልተገኙም ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም ነቢዩ አዳዲስ የቁጥሮችን መገለጦች በአንዳንድ ምዕራፎች ላይ እንዲጨምር ይመራ ነበር፡፡ ስለዚህም ምዕራፎቹ በዚያን ጊዜ በሚገባ የተደራጁና ስም የተሰጣቸውም የነበሩ ሲሆን እነዚያኑ ስማቸውንም አሁንም እንደያዙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ምዕራፎች የሚቀናበሩበት ምንም የተወሰነ ስርዓት ወይንም ቅደም ተከተል ያልነበረ ይመስላል፡፡ እያንዳንዱም የሰጠው የራሱን ሙሉ ጽሑፍ ማለትም የራሱን ቁርአን ነበር፡፡ የቁርአንን ጥቅሶች በቃል የማስታዎስ ጥረት የመሐመድ ትጉ ተከታዮች የፍቅር ውጤት ብቻ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የክብርና የመብትም የትርፍም ምንጭ ሆኖ ነበር፡፡ ስለዚህም እነዚያ ብዙ ጥቅሶችን ያስታወሱት በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የኢማምነትን ቦታ ወይንም የአደባባይ የአምልኮ መሪነትን ቦታ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎቹ ሙስሊሞችም ይልቅ ከምርኮ የሚገኘውን ከፍተኛ ድርሻ እንዲሰጣቸውም እነሱ ጥያቄን ያቀርቡ ነበር፡፡
መሐመድ ከሞተ በግምት ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ከቡካሪ እንደምንማረው፤ ቁርአን ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ላይ እንደ አንድ ሙሉ ጽሑፍ ተጠናቀረ፡፡ ይህም በአቡበከር ትዕዛዝ አማካኝነት ሲሆን የተደረገውም በዛይድ ኢብን ታቢት ነበር፡፡ እርሱም ከመሐመድ ጓደኞች አንዱና የጽሑፍ ገልባጭ (ቀጂ) ነበር፡፡ ለዚህ እርምጃ ዋና ምክንያት የነበረው የቁርአን ብዙዎቹ ቀሪዎች (አስታዋሾች) በያማማ (በሂጂራ 12) ጦርነት ላይ መሞታቸውን ዑማት ብኑል ካታብ በማስተዋሉ እና መገለጡ በከፊል ወይንም በሙሉ ይጠፋል በማለት ፈርቶ ስለነበር ነው፡፡ ስለዚህም የተበታተኑት ሱራዎች (ምዕራፎች) አንድ ላይ መሰብሰብና ስልጣን ባለው መንገድ በጽሑፍ መልክ መቀመጥ ያለባቸው መሆኑን እርሱ ካሊፋውን በጣም አጥብቆ አሳሰበው፡፡ ነቢዩ እራሱ ተገቢ ነው ብሎ ያልተሰማውን ነገር ለማድረግ ዛይድ በመጀመሪያ ላይ በጣም አመንትቶ ነበር፤ ነገር ግን በመጨረሻ ላይ ለካሊፉ ትዕዛዝ ታዘዘ፡፡ ታሪኩም በእርሱ በራሱ አንደበት የተነገረው እንደሚከተለው ነው፡ ‹አቡ በከር ለእኔ እንደዚህ አለኝ ‹አንተ የተማርክ ወጣት ሰው ነህ፣ አንተን አንጠራጠርም፣ አንተ ለእግዚአብሔር ሐዋርያ የመለኮትን መገለጥ የመጻፍ ልማድ ነበረህ፡፡ ስለዚህም ቁርአንን ፈልግ፤ ሰብስበውም፡፡› አለኝ፡፡ ተራራን የማንቀሳቀስን ተግባር በእኔ ላይ ጣሉብኝ፣ ነገር ግን ቁራንን እኔ እንድሰበስብ ሃላፊነት ከሰጡኝ ሰዎች በላይ በእኔ ላይ በጣም አይከብድብኝም፡፡ አቡ በከርም እኔ እንድሰበስብ ከማደፋፈር ወደ ኋላ አላለም፡፡ ይህም እግዚአብሔር ኡማርና አቡበከር በልባቸው ግልፅ ሆኖላቸው ለእኔ ግልፅ እንዳደረጉት የእኔንም ልብ ግልፅ እስካደረገው ድረስ አቡ በከር እኔን ከማደፋፈር አላቋረጠም፡፡ ስለዚህም እኔ ቁርአንን ሙላውን ከፓልም ቅጠል፣ ቅጠል ከሌለው የፓልም ቅርንጫፍ፣ ከነጭ ድንጋዮችና ከሰዎች ልብ ውስጥ ሰበሰብኩኝ፡፡ ይህም በአቡ ኩዛይማህ የአንሳሪው ዘንድ የሱራቱ ታባህን መደምደሚያ (ምዕራፍ 9 ቁጥር 129) እስካገኝ ድረስ ነበር፡፡ አገኘሁት፣ ያገኘሁትም ከሌላ ከማንም ዘንድ አይደለም›፡፡
ዛይድ በስራው ፍፃሜ ላይ ጥራዙን ለአቡ በከር አስረከበ፣ ይህም በኩፊክ የጽሑፍ ዓይነት ተጽፎ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አቡ በከርም እስከ ሞቱ ድረስ በጥንቃቄ አስቀምጦታል፡፡ ሲሞትም ለኡማር ተላልፏል እሱም ከሞተ በኋላ በሐፍሳ በልጁ እጅ እንዲቀመጥ ተደርጓል፣ እሷም ከመሐመድ የሙት ሚስቶች መካከል አንዷ ናት፡፡ ሌሎች የምዕራፍ ቅጅዎች ከዚያ በኋላ ተደርገዋል እነሱም ከዚህኛው ወይንም ዛይድ ከተጠቀመባቸው ከመጀመሪያዉ ምንጮች ማለትም ተቀባይነት ካላቸው ላይ የተዘጋጁ ናቸው፡፡
ቁርአን በቃል እየተቀራ እያለ ቀስ በቀስ ስህተቶች ወይንም ቢያንስ ልዩነቶች በቁርአን ጽሑፎች ውስጥ ገብተዋል፡፡ እንዲሁም በእነዚህ ቁርጥራጭ ቅጂዎችም ውስጥ እንደዚሁ ገብተው ሊሆን ይችላል፡፡ ዛይድ እንዲደረግ እንደጻፈው ያለ ሁሉንም የሚዳኝ (ሥልጣን ያለው) አንድ ቅጂ እንዲኖር አቡ በከር ያሰበ አይመስልም፣ ምክንያቱም በተፈጥሮ ያሉትን የልዩነቶች መኖር ሊቃረን አይችልምና፡፡ እንዲሁም በአብዛኛው ወይንም በአጠቃላይ ሆነ ተብለው የሚደረጉ አይደሉምና፣ ለዚህም ቁርአን እንደሌሎቹ ስራዎች ሁሉ በቃል የሚተላለፍ ሊሆን ይችል ነበርና፡፡ በዚያን ጊዜ የተለያዩ የአረብኛ አባባሎች ነበሩ፣ በመጀመሪያም ደረጃ አንዳንድ ቃላቶችን የመግለጥ (የመተርጎም) ዝንባሌ መኖር ነበረበት፣ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እነዚህን የልዩ ልዩ አባባሎችን አጭር ማብራሪያዎች በሚታወሱት ጥቅሶች ውስጥ የሚገቡበት መንገድን መፍቀድ ነበር፡፡ እነዚህ ደግሞ በጣም ለተሰጡት ሙስሊሞች አዕምሮዎች የሚፈጥሩት መምታታትና ግራ መጋባት ቀላል አልነበሩም፡፡ በመጨረሻም ኡስማን አርመኒያንንና አዛርባጃንን ይዋጋ በነበረበት ጊዜ በሁዳይፋህ ኢብኑ ያማን ያለውን አደጋ አስመልከቶ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው፡፡ እርሱም የመጀመሪያው እንደዚህ እጅግ በጣም የተበላሸ ካልሆነ በስተቀር ያለውን አደጋ አስመልክቶ፡፡ ቡካሪ ሁዳይፋህ ለኡስማን ያለውን እንደሚከተለው ይነግረናል፡ ‹የታማኞቹ አዛዥ ሆይ፣ እነዚህን ሰዎች አስቁማቸው አይሁዶችና ክርስትያኖች እንደሚያደርጉት ስለመጽሐፉ በመካከላቸው ልዩነቶችን ከማንሳታቸው በፊት አስቁማቸው›፡፡ ከዚያም ካሊፉ ወደ ሐፍሳ የመጀመሪያውን ቅጂ ወደ እርሱ እንድትልክ እርሱም እንዲቀዳና ቅጂውም እንደተፈፀመ እንደሚመለስላት ቃል ገብቶ እንድትልክለት እንዲጠይቅ መልክተኛን ላከ፡፡ ከዚያም እንደገና የማጣራት ስራን እንዲሰሩ (የተሻለ ስራ እንዲሰራ) ለማድረግ ዛይድንና ከመሐመድ ከራሱ ጎሳ፤ ከኩራይሽ የነበሩትን ሦስት ሰዎች አብሮ መደበ፡፡ ቢያንስ የእሱ ቋንቋ ሊያስተላልፍ የፈለገው የሚመስለው ይህንን ነበር፣ ምክንያቱም ለሦስቱ ኩራይሾች የተናገረው የሚከተለውን ነውና፡ ‹እናንተና ዛይድ ኢብን ሳቢት፣ በማንኛውም የቁርአን ክፍልን በተመለከተ በምትለያዩበት ጊዜ በኩራይሽ አባባል (ዲያሌክት) ጻፉት፣ ምክንያቱም ቁርአን የተገለጠው በእነሱ በራሳቸው ቋንቋ ነውና›፡፡ እኛ የተነገረን አዲሱ ክለሳ ከመጀመሪያው ላይ የተቀዳ ነበር ተብሎ ነው፣ በአብዛኛው ክፍል እንደዚህ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው ቃላት እንደሚመሰክሩት ከሆነ አንዳንድ ለውጦች እንደተደረጉ ነው፣ ምንም እንኳን በመልካም እምነት እንደተደረጉ ባያጠራጥርም፣ በቅድሚያም የመካን ዲያሌክት በመጽሐፉ ውስጥ ለመጠበቅ ተብሎም ነው፡፡ አንዳንድ ለውጦች የመደረጋቸው ሌላው ማስረጃ ዛይድ በዚህ ሁኔታ ላይ በመጀመሪያው ቅጂ ወቅት ያልነበረ ጥቅስ በዚህ ሁኔታ ላይ እንደገና መሰብሰቡን ከሰጠው መግለጫ ላይ ነው፣ እሱም እራሱ መሐመድ ጥቅሱን ሲናገረው የሰማው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ይሁን እንጂ እርሱ፤ እራሱ በራሱ ስልጣን ጥቅሱን ሊጨምረው አልደፈረም፣ ነገር ግን ይህንን ጥቅስ በቃሉ ማስታዎስ የሚችለውን ሰው ፈለገ፡፡ ይህም በሆነ ጊዜ ጥቅሱ በምዕራፍ (በሱራቱል) አህዛብ ውስጥ ተጨመረ፡፡ ከዚያም ኡስማን ጽሑፎቹን ለሐፍሳ መለሰላት፣ ከዚያም ከዚህ ጋር ተመሳስሎ አንድ ዓይነት ያልሆነው ቅጅ ሁሉ እንዲቃጠል ከሚያዝ ትዕዛዝ ጋር - ለእያንዳንዱ አገር የቅጃቸውን ምሳሌ ቅጂ ላኩት፡፡
የመጨረሻው አካሄድ ለእኛ ፍትህ አልባ ሊመስለን ይችላል፣ ነገር ግን የቁርአንን ጽሑፍ ከዚያን ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በመሐመዳውያን እጅ በአንድ መንገድ ብቻ እንዲገኝ አድርጎታል፡፡ ከኡስማን ትዕዛዝ ተግባራዊ መሆን በኋላ በማንኛውም ጠቃሚ ሁኔታዎች ከተከለሰው ቅጂ የሚለየውና አንድ ብቻ የነበረው የሐፍሳም ቅጂ እንኳን፣ በዚያን ታሪክ ላይ በማርዋን ጊዜ ተቃጥሏል፡፡ በጣም ትጉ በሆነ ምርመራ የሚገኙት በጣም ጥቂት የሆኑት ልዩነቶች በተለያዩ የቁርአን ቅጂዎች ላይ አሁንም ይገኛሉ፡፡ እነሱም በነጥቦች አቀማመጥ ላይ ከሞላ ጎደል በሁሉም ላይ ይገኛሉ ይህም አንዳቸውን ከሌላኛው በሚለይ መልኩ ነው፡፡ ለዚህም ከጥንታዊው የኩፊክ ቋንቋ የተለየ ምልክት ያላቸውን የተወሰኑ ፊደሎችን ማንሳት ይቻላል፡፡
ስለዚህም እኛ እንድንደመድም የምንመራው መሐመድ የተወው አይነት ቁርአን አሁንም እንዳለን ነው፡፡ እናም ስለዚህ ፍፁም በሆነ እርግጠኝነት ጽሑፎቹ ትክክለኛነት ያላቸው መሆኑን፣ ይህም እርሱ ምን እንዳስተማረና የተለያዩ አስተምህሮዎችን (ዶክትሪኖችን) ዓረፍተ ነገሮችን ከየት እንዳመጣቸው ተገንዝበን፤ በቁርአን ውስጥ የሚገኙትንና በልማድ ውስጥ የተገለጡትን እንዲሁም የተብራሩትን ከዚያም እስልምና የሚባለውን ሃይማኖት የሰጡትን ለማወቅ መጽሐፉን ለማጥናት መቀጠል እንችላለን ማለት ነው፡፡
የእስልምናን ምንጭ መነጋገርን በተመለከተ በመጀመሪያ ደረጃ በሙስሊሞች መካከል ታዋቂ በሆኑ አስተማሪዎች፤ የሕግ ዶክተሮች የተነገሩትን አረፍተ ነገሮች መመልከት በጣም ትክክል ይሆናል፡፡ የእነሱም አመለካከቶቻቸው በዚህ ነጥብ ላይ በቁርአን በራሱ የተደገፈ ለመሆኑ እንመረምራለን፡፡ ከዚያም እኛ የምናልፈው እነዚህን አረፍተ ነገሮች ለተሰጡት ጉዳዮች እንደ ትክክለኛ መግለጫዎች አድርገን ልንቀበላቸው እንችላለን ወይ? የሚለውን ወደ መመርመር እንሻገራለን፡፡
የእስላም ዑላማዎች ቁርአን እራሱ የእግዚአብሔር ቃል ነው በማለት ማረጋገጣቸው፤ ሁልጊዜም ይህንን ማረጋገጣቸው በጣም የታወቀ ነገር ነው፡፡ ይህም ታላቁ እግዚአብሔር በሰማይ ባለው ‹በተጠበቀው ማህደር›፣ ‹ታብሌት› ላይ ጽፎ ገና ከዓለም መፈጠር በፊት ድሮ እንዳስቀመጠው ነው፡፡ በካሊፍ አል-ማሙን ጊዜ (ሂጂራ 198-218 ማለትም በ813-33 ዓ.ም) እና ከዚያም በኋላ ‹ቁርአን ዘላለማዊ ነው በሚሉትና ቁርአን የተፈጠረ ነው› በሚሉት መካከል እጅግ በጣም መራራ ክርክሮች ተደርገውም ቢሆንና፣ እንዲሁም አሁን በዚያ ውስጥ መግባታችን አስፈላጊያችን ባይሆንም እንኳን፣ ነገር ግን ሙስሊሞች በሙሉ የሚስማሙት ሁልጊዜ መጽሐፉ በመሐመድ የተቀናበረ እንዳልሆነና ወይንም በማንኛውም ሰዋዊ ጸሐፊ እንዳልተጻፈ ነው፡፡ በሌላው ጎኑ ደግሞ እነሱ የሚያምኑት እርሱ ሙሉ ለሙሉ የእግዚአብሔር የራሱ ስራ እንደሆነ ነው፡፡ መሐመድም በቀላሉ የእሱ መልእክተኛ እንደሆነ ነው የእርሱም ስራ የነበረው የመለኮትን መጽሐፍ መቀበልና እርሱንም ለሰዎች ማስተላለፍ እንደነበረ ነው፡፡ ልማድ የሚነግረን ደግሞ መጽሐፉ በአንድ የተለየ ሌሊት እንደወረደ ነው ይህም ከከፍተኛው ሰማይ ወደ ዝቅተኛው ሰማይ በመላእክት አለቃው በገብርኤል፣ እርሱም ከዚያ በኋላ ቀስ በቀስ ጥቅሶችንና ምዕራፎችን ለመሐመድ አዕምሮና ምላስ እንዳወረደው ነው፡፡ ስለዚህም ቁርአንን በተመለከተ ሰዋዊ የሆነ ምንም ነገር የለም፣ እርሱም ሙሉ በሙሉ እና ሞላውን የመነጨው ከመለኮት ብቻ ነው፡፡
ማለትም የእኛ አንባቢዎች ሊገነዘቡ የሚገባቸው ነገር በትክክለኛዎቹ የመሐመዳውያን ዘንድ ስለ ቁርአን ያለው አመለካከት ይህ እንደሆነ ነው፡፡ እዚህ ላይም እኛ ይህንን በተመለከተ (በዚህ ጉዳይ ላይ) ሁለት አንቀፆችን በጣም ታዋቂ ከሆነው የአረብ ጸሐፊ ኢብን ካልዱን ላይ እንጠቅሳለን ‹ስለዚህም ይህንን እወቁ› አለ፣ ‹ቁርአን የወረደው በአረቦች ቋንቋ ነው እንዲሁም በእነሱ የአነጋገር ስነ-ዘዴ ላይ ተመስርቶ ነው፣ እናም ሁሉም በእርሱ የተለያየ ክፍል ላይ ያሉትን ልዩ ልዩ መልእክቶች እርስ በእርስ ባላቸው ግንኙነቶቻቸው ገብቷቸዋል አውቀዋቸዋልም፡፡ እርሱም ክፍል በክፍል እንዲሁም በጥቅሶች ቡድን እየሆነ መውረዱን ቀጠለ፣ ይህም የእግዚአብሔርን አንድነት ዶክትሪን እና የሃይማኖትን ግዴታዎች ለመግለጥ ነው፣ ይህም ሁኔታዎች እንዳስፈለጉት ሆኖ ነው፡፡ የእነዚህ አንዳንዶቹ ጥቅሶች የእምነት አንቀፆችን የያዙ ናቸው አንዳንዶቹም ደግሞ ባህርይን ለመምራት የሚያስፈልጉ ትዕዛዞች ናቸው›፡፡ ይኸው ጸሐፊ በሌላ አንቀፅ ውስጥ የሚከተለውን ተናግሯል፡ ‹ይህ ሁሉ ለአንተ ማረጋገጫ ነው፣ ያም ከመለኮት መጽሐፍ መካከል በእርግጥ ቁርአን ነበር ማለትም የእኛ ነቢይ (የእግዚአብሔር በረከትና ሰላም በእሱ ላይ ይሁንና) የተገለጠለት ነው፣ ይህም እንደሚቀራ (እንደሚታወስ) መልክ በመሆን ልክ በቃሎቹና በክፍሎቹ ውስጥ እንዳለው ሆኖ ነው፡፡ በሌላ ጎኑ ግን ሕግና ወንጌል እንዲሁም ሌሎቹ ሰማያዊ መጻሕፍት ለነቢያት የተገለጡት በሐሳቦች መልክ ሆነው ነበር፣ ያም እነሱ በእራሳቸውን በሳቱበት ሁኔታ ውስጥ እያሉ በነበረበት ጊዜ ነበር፣ እነሱም ወደ ሰው ትክክለኛ ሁኔታ ከተመለሱ በኋላ እነዚያን በራሳቸው ልማዳዊ ቋንቋ ገለጧቸው (አስረዱ)፣ ስለዚህም በእነሱ ውስጥ ምንም ተዓምራዊ ነገር የለም፡፡› ማለትም ‹የእስላም ዑላማ፣ ሌሎች ነቢያት ከመሐመድ በፊት መምጣታቸውን እንዲሁም መለኮታዊ መልእክቶችን መናገራቸውን ቢቀበሉም፣ የያዙት አመለካከት ግን የቁርአን መገለጥ ከሌሎቹ ቅዱሳን መጻሕፍት የተለየ ነው፤ ይህም በደረጃው ብቻ ሳይሆን በዓይነቱም ነው፣ ለምሳሌም ያህል ሕግና ወንጌል ከመጡበት ሁኔታ የተለየ ነው፡፡ የእነዚህ መጻሕፍት ጸሐፊዎች አንዳንድ ሐሳቦችን ከእግዚአብሔር በአንድ በሆነ መንገድ ተቀብለዋል፤ ነገር ግን ከዚያ በኋላ እነዚያን ሐሳቦች ለመግለጥ እነሱ የተጠቀሙባቸው ቋንቋዎች የእራሳቸው ነበሩ፣ ስለዚህም እነሱ ከእነሱ (ከሰው) በላይ ነው የመጡት ማለትም መለኮታዊ ናቸው በማለት ሊናገሩ አይችሉም፡፡ በአንፃሩ መሐመድ ግን ገብርኤልን ጮክ ብሎ ሲያነብ ወይንም እሱ በግልጥ እያንዳንዷን የቁርአንን ቃል በሚሰማ መንገድ ሲቀራ (ሲያስታውስ) ሰምቶታል፣ ይህም እሱ በሰማይ በተጠበቀው ገበታ ላይ እንደተጻፈው ነው፡፡ አረብኛም የሚወሰደው የሰማይ ቋንቋ እና የመላእክት ቋንቋ ተደርጎ ነው ስለዚህም በቁርአን ውስጥ እነዚያ ቃላቶች እራሳቸውን እናገኛለን፡፡ እኛም በቁርአን ውስጥ ያለን፡- ቃሉን፣ የራሱን የእግዚአብሔርን ቃል ነው፡፡ የቁርአን ቃሎች አምሳሌዎች፤ ገለጣዎች፤ ታሪኮች፤ የአቀራረብ ዘዴዎች ሁሉም ሙሉ በሙሉ የመለኮት ምንጭ ያላቸው ናቸው፡፡
ይህ አመለካት እራሱ ከቁርአን ዓረፍተ ነገሮች ጋር ሙሉ ለሙሉ የሚስማማ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር አይኖርም፡፡ የመለኮት ምንጭነቱ ‹አላህ የሚሻውን ያብሳል ያጸድቃልም የመጽሐፉ መሠረትም እርሱ ዘንድ ነው› (ቁርአን 13.39)፡፡ እንደገናም ደግሞ እንዲህ ዓይነቶቹ አባባሎች በቁርአን ውስጥ በተለያየ መንገድ እንደሚከተለው ይገኛሉ ‹ይልቁንም እርሱ የከበረ ቁርአን ነው፣ የተጠበቀ በኾነ ሰሌዳ ውስጥ ነው› (ቁርአን 85.21፣22)፡፡ ቁርአን የሚለውም ቃል እራሱ ይህንን ያመለክታል ‹ያ በቃል የተታወሰ› (በቃል የተቀራ)፡፡ በሌላ ቦታም ታላቁ እግዚአብሔር መሐመድን እንዲናገር እንዳዘዘው እናነባለን ‹በምስክርነት ከነገሩ ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ማነው? በላቸው (ሌላ መልስ የለምና) አላህ ነው፤ በእኔና በናንተ መካከል መስካሪ ነው፣ ይህም ቁርአን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ፣ ከአላህ ጋር ሌሎች አማልክት መኖራቸውን እናንተ ትመስክራላቸሁን? በላቸው እኔ አልመሰክርም በላቸው እርሱ አንድ አምላክ ብቻ ነው እኔም ከምታጋሩት ነገር ንፁህ ነኝ› (ቁርአን 6.19.) እንዲሁም ደግሞ ቁርአን 47.1 ተመልከቱ ቁርአን ላይ ያለውን ንግግር በተመለከተ እግዚአብሔር እንደተናገረ ሲጠቀስ ይታያል፣ ‹እነዚያ የካዱ ከአላህ መንገድም የከለከሉ (አላህ) ሥራዎቻቸውን አጠፋባቸው›፤ እንደዚህ ዓይነት ማገናዘቢያዎች ያለማቋረጥ ሊጠቀሱ ይቻላል፡፡ ቁርአን 4.84፤ 17.107፤ 46.7፤ 53.4 ወ.ዘ.ተ፡፡
ስለዚህም ስለ ቁርአን ምንጭ የመሐመዳውያን ገለፃ፣ የተመሠረተው በስተመጨረሻ በቁርአን ላይ እንደሆነው ሁሉ፣ የእስላም ሃይማኖት ብቸኛ ምንጭ እና መገኛ ቁንጮ የሆነው እራሱ እግዚአብሔር ነው በማለት ነው፡፡ ስለዚህም ቁርአን ምንም የሰው ምንጭ የለውም እንዲሁም የእርሱ አንዲትም ክፍል እንኳን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ከጥንታዊ መገለጦች አልመጣም እንደዚሁ ወይንም ከሌሎች ሃይማኖቶችም ሁሉ፣ ምንም እንኳን እርሱ የተገለጠው ሕጉንና ወንጌልን ለማረጋገጥ ቢሆንም፣ እንዲሁም ከእነሱ ያልተበከለ እና የመጀመሪያ መገለጥ ጋር እንደሚስማማም ቢናገርም ነው (ቁርአን 57.26)፡፡
የዩሮፕ አንባቢዎች እንዲህ ዓይነቱ የእስልምና ምንጭ በአጠቃላይ እንዲሁም ቁርአንን በነጠላ ለመቀበል እጅግ በጣም ማስረጃን ይፈልጋሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አመለካከት መሠረት ቁርአንን በመጀመሪያ አረብኛው ማንበብ የማይችሉት እነዚያ ቁርአንን በተለያዩ የዩሮፕ ቋንቋዎች (ለኛ አገር ያለውን የአማርኛውንም ትርጉም) ትርጉሞችን በማንበብ አስተምህሮውን ለመመርመር ችለዋል፡፡ በጣም የታወቀውም የእንግሊዝኛ ትርጉም ደግሞ በሮድዌል እና ፓለመር የታተመው ነው፣ (የአማርኛው ደግሞ በነጃሺ ማተሚያ የታተመው ነው)፡፡ እኛ አሁን እየተመለከትነው ያለው አባባል ለሚያስተውል አዕምሮ እራሱን በራሱ የሚቃወም ነው፡፡ ከዚህም በላይ የቁርአን የስነ ምግባር ተቋም፣ ቁርአን ያቀረበው የመለኮት ባህርይና ተፈጥሮ አመለካከት፣ ቁርአን ከጊዜው ጋር የማይሄድ መሆኑ፣ እንዲሁም የቁርአን እጅግ በጣም ብዙ ችግሮቹ (ስህተቶቹ) የመሐመድ የእራሱ ቅንብር የመሆኑን ነገር እንድንጠራጠረው ያስደርጉናል፡፡ የቁርአን ምዕራፎች በታሪካዊ የአቀነባበር ቅደም ተከተላቸው እንዲደራጁ ሲደረጉ፣ እና ከመሐመድ ሕይወት ክስተቶች ጋር ሲነፃፀሩ የምንመለከተው ነገር - ሙስሊሞች መገለጥ ነው የሚሉት መገለጥ እንዳልሆነ በጣም ብዙ እውነቶችን ልንመለከት እንችላለን፡፡ ስለዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተቀናበሩ ናቸው፣ አንዳንድ ጊዜም መሐመድ ለሚያደርገው አዳዲስ የማፈንገጥ ሐሳቦች ማፅደቂያ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ቁርአን የጸሐፊው ሕይወትና ባህርይ ታማኝ የሆነ መስተዋት ነው፡፡ ቁርአን የምድረ በዳውን አየር ያነፍሳል፣ የነቢዩ ተከታዮች በጦርነት ላይ ለጥቃት መጀመሪያ ሲፈጥኑ የሚያሰሙትን ጩኸት ያስደምጠናል፣ እርሱ የመሐመድ የራሱ አዕምሮ እንዴት ይሰራ እንደነበር ይገልጥልናል፣ እንዲሁም እርሱ ምንም እንኳን ባለራዕይ ቢሆንም ከእውነተኛ ትሁት ሰው - የእርሱ ባህርይ ቀስ በቀስ ወደ ንቁ አጭበርባሪ እና ግልጥ ስጋዊ ስሜታዊነት ማሽቆልቆሉን ያሳየናል፡፡ ያለምንም ትምክህት እንዲሁም በግልጥነት መጽሐፉን ለሚያነቡ ሰዎች እነዚህ ሁሉ በጣም ግልጥ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት ጥያቄው እራሱን ያቀርባል፣ ታሪኮችን፣ መመሪያዎችን፣ እርሱ በጀመረው ሃይማኖት ውስጥ ያካተታቸውን ሐሳቦቹን፣ መሐመድ የተበደረው መቼ ነበር? ከእነዚህ ውስጥ የእርሱ የራሱ ፈጠራዎች የትኞቹ ነበሩ፤ ከእነዚህስ ውስጥ ከቀደሙት ስርዓቶች ውስጥ የተወሰዱት የትኞቹ ነበሩ? ከእራሱ ሃይማኖት ውጪ እንደሆኑ ከተናገሩት ውስጥ እንደ ማስተማሪያ አድርጎ የተጠቀመባቸው ምን ያህሎቹን ነው? እርሱ ከሌሎች ስርዓቶች ተበድሮ የነበረ ከሆነ በየትኛው የቁርአን ልዩ ክፍል ነበር? የየትኛው የሃይማኖት ስርዓት፣ ምን ሐሳብና ታሪክ፣ ለእንደዚህ ዓይነት ምንጮች ምን ዓይነት ትዕዛዞች (የፍርድ ቤት ማገጃ) ተፈልገው ሊገኙ ይችላሉ? ከውጤቶቹም ውስጥ ከመሐመድ ከራሱ ባህርይ እንዲሁም ከእርሱ ከነበረበት ሁኔታ የተነሳ የመነጩት ምን ያህሉ ናቸው? አንዳንዶቹ ችግሮች እነዚህን ይመስላሉ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምናያቸው ዋና ዒላማዎች በግልፅና እጥር ምጥን ባለ መንገድ በተቻለ መጠን ለማየት የምንፈልጋቸው፡፡ ምርምሩን ከየትኛውም የአመለካከት ነጥብ አኳያ እንውሰደው፣ አስገራሚ መሆኑን ሊቀንስ አይችልም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምርመራ በእውነት ከተከታተልነው አንድን ሙስሊም የአባቶቹን እምነት በእራሱና በትክክለኛ እሴቱ ምን እንደነበረ እንዲያደንቅ ሊያስችለው ይችላል፡፡ አንድ የንፅፅር ሃይማኖት ተማሪ ደግሞ የአንድ ጎሳ ሃይማኖት በአሁኑ ታሪካዊ ወቅትም እንዴት ሊነሳ እንደሚችል ትንተናን መውሰድ ይችላል፡፡ እርሱም ብልህ ከሆነ ከነጠላ ክስተቶች ላይ ተነስቶ ችኩል መደምደሚያን ሊያደርግ አይችልም፡፡ የክርስትያንም ሚሽነሪዎች የእኛን ምርመራ ጠቃሚ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ፣ ይህም በእነሱ ውስጥ ጠያቂ ለሆኑ ሙስሊሞች የማይደፈረውን አቋማቸውን እንዲያዩ ለማስቻል አዳዲስ ዘዴዎችን ሊያገኙባቸው ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ሁሉ ነገሮች (ምልክታዎች) ወደጎን በመተው እኛ በመመርመር የምንገፋበት ነገር የቁርአን የመጀመሪያዎቹ ምንጮች በእውነት ምን እንደነበሩ ነው፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡
ቁርአን ስለ እራሱ፣ የእስልምና ተከታዮች፣ የእስልምና ምሁራን እና ሊቃውንት ሁሉ ስለ ቁርአን የሚናገሩት ነገር እጅግ በጣም ከፍ ያለ ነገርን ነው፡፡ አዎ በእነርሱም አባባል መጽሐፉ ከሰማይ የወረደ መለኮታዊ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ያለውን ጽሑፍ በምርምር ያቀረበው ሰው የሚለው ቁርአንን በቅን አዕምሮ የሚያነብ ሰው የሚደርስበት መደምደሚያ በጣም የተለየ እንደሚሆን ነው፡፡
አንባቢዎች ሆይ በቅን ልብና ነገሮችን በእውነት ለመረዳት ጉጉት ያለው አዕምሮ ይዞ መገኘት በጣም ጠቃሚ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ስለዚህም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ያሉትን ተከታታይ ምርመራዎች በጥሞና እንድትከታተሉ እንጋብዛችኋለን፡፡ የቁርአንን ምንጭ በትክክል መገንዘብ ዘላለምን የት ልታሳልፉ እንደሚገባችሁ የሚጠቁማችሁ እውነታ እንደሚኖረው አንጠራጠርም፡፡ ይህንንም በማድረግ ላይ እያላችሁ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታነቡ እና ነገሮችን እንድታመዛዝኑ እንጋብዛችኋለን፡፡
እግዚአብሔር በፀጋው ይርዳችሁ፡፡
የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN
ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ