የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ምዕራፍ አራት ክፍል ሦስት

የጌታ ኢየሱስ ልጅነትና የማዕዱ ታሪኮች  

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

ከአሁን በፊት በተነገረው ውስጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርአን የሚያስተምረውን አንድ ነገርን ተምረናል፡፡ አሁን ግን ነገሩን ሰፋ ባለ መንገድ አሁን እንየው፡፡ በቁርአን 3.46፣48 ላይ የተመዘገበልን ነገር ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት መልአክ ስለ እርሱ እንዲህ እንዳለ ነው ‹በሕፃንነቱና በከፈኒሳነቱ ሰዎቹን ያነጋግራል ከመልካሞቹም ነው (አላት) ... ጽሕፈትንና ጥበብንም ተውራትንና ኢንጂልንም ያስተምረዋል፡፡› በቁርአን 19.29-31 ላይ ደግሞ ከዚህ በፊት እንዳየነው ሁሉ የድንግል ማርያም ሰዎች እርሷን በገሰጧት ጊዜ ወደ ልጁ እንደጠቀሰችና እርሱን ስለ አፈጣጠሩ እንዲጠይቁት እንዳደረገች ነው፡፡ እነርሱም በመደነቅ ‹በአንቀልባ ያለን ሕፃን እንዴት እናናግራለን አሉ!› እንዲሁም ደግሞ፡ ‹(ሕፃኑም) አለ እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ መጽሐፍን ሰጥቶኛል ነቢይም አድርጎኛል በበየትም ስፍራ ብኾን ብሩክ አድርጎኛል በሕይወትም እስከ አለሁ ሶላትን በመስገድ ዘካንም በመስጠት አዞኛል› በማለት ተናግሯል፡፡

የዚህንም ተረት ምንጭ ተፈልጎ ከመገኘት በጣም ሩቅ አይደለም፡፡ እንዳየነው ሁሉ ከአፖክሪፋዊ ወንጌሎች አንዱ ክርስቶስ ወደ ግብፅ በነበረበት ጉዞ ላይ ህፃን ሆኖ የነበረውን ሁኔታ መዝግቦታል፣ እዚያም እናቱ ከእርሱ ላይ ፍሬን እንድትቀጥፍ እንዲፈቅድላት ጎንበስ እንዲል የዘንባባ ዛፍን እንደተናገረው ተመዝግቧል፡፡ ነገር ግን መሐመድ ይህንን የራሱን ክስተት የተበደረበት ምንጭ በጣም የሚታወቀው ‹የሕፃንነት የአረብ ወንጌል› በመባል ነው፡፡ በዚያም በመጀመሪያው ምዕራፍ ውስጥ እንደሚከተለው እናነባለን፡-

‹ይህንን በሊቀ ካህኑ በጆሴፈስ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ አግኝተነዋል፣ በክርስቶስ ዘመን በነበረው (ሰዎችም እርሱ ቀያፋ ነበር ይላሉ)፣ ያም ሰው የተናገረው ኢየሱስ በአንቀልባ ታዝሎ በነበረ ጊዜ ተናግሯል በማለት ነው፣ እንዲሁም ለእናቱ ለማርያም አላት፣ ‹በእውነት እኔ ኢየሱስ ነኝ የእግዚአብሔር ልጅ አባቴም የላከኝ ለዓለም መዳን ነው›፡፡

ይህ አፖክሪፋዊ ወንጌል ለእርሱ የተናገረውን ነገር እንዳየነው በእርግጥ መሐመድ ክርስቶስን ሊወክል አይችልም፣ ምክንያቱም በቁርአን ውስጥ የክርስቶስ መለኮታዊ ልጅነት በየትም ቦታ ላይ ተክዷልና፡፡ ስለዚህም ኢየሱስ ሕፃን ሆኖ እንደታዘለ መናገሩን እያመነና እየጠቀሰ መሐመድ በታሪኩ ውስጥ በክርስቶስ አንደበት ውስጥ ያስቀመጠው ከእራሱ ሐሳብ ጋር በጣም የሚስማማውንና ከእስልምና ጋር ሊሄድ የሚችለውን ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ታሪኩ አንድ ዓይነት ነው፡፡

ይሁን እንጂ የዚህ የአረብኛ አፖክሪፋዊ ወንጌል አቀራረብ በጣም መጥፎ ነው ስለዚህም በመሐመድ ጊዜ ነበር ብሎ ለማመን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እንዲሁም ቢሆን እንኳን ስራው በመጀመሪያ የተቀናበረበት ቋንቋ አረብኛ ሊሆን በፍፁም አይችልም ይህ ደግሞ በጣም ትንሽ ነገርና ጥቂት ውጤት ያለው ነው፡፡ መጽሐፉ ሲጠና በመጀመሪያ ከተጻፈበት ከኮፕቲክ ወደ አረብኛ ለመተርጎሙ ጥቂት የመጠራጠሪያ ክፍተት ይገኛል፡፡ ይህም መሐመድ ከተረቱ ጋር በምን ዓይነት መንገድ እንደተገናኘ  በጣም የሚገልጠው ክፍል ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የግብፅ ክርስትያን ገዢ ለመሐመድ ሁለት የኮፕቲክ ልጃገረዶችን በስጦታ እንደሰጠው በሚገባ የታወቀ እውነታ ነውና ከእርሱም ውስጥ አንዷ፡ ‹ማርያም ኮፕታዊቷ›፣ ከቅምጦቹ ውስጥ በጣም ተወዳጅ የሆነችው ቅምጡ ሆና ነበር፡፡ ይች ልጅ ምንም እንኳን ከወንጌል ጋር በሚገባ የማትተዋወቅ ቢሆንም ያለምንም ጥርጥር በዚያን ጊዜ በጣም ታወቂ በሆነው ‹በሕፃንነት ወንጌል› ውስጥ ያሉትን ተረቶች በሚገባ ታውቃቸው ነበር፡፡ መሐመድም ይህንን ተረት የተማረው ከእርሷ ሳይሆን አይቀርም፣ ከዚያም እርሱ በክርስትያኖች ሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ባለው ወንጌል ውስጥ እንዳለና ከእግዚአብሔር የመጣ እንደሆነ አድርጎ ቆጥሮት ነበር፣ ስለዚህም በዚህ መሰረት ነው በቁርአን ውስጥ መሐመድ ያካተተው፡፡ በእርግጥ ከማርያም ሌላ ይህንን የኮፕቲክ ተረት ለመሐመድ የነገሩት ሌሎች ሰዎች ሊኖሩት ይችላሉ ነገር ግን ማንም ይሁን ማን የነገረው ወይንም የነገሩት የተዓምራዊው ታሪክ ምንጭ ከዚህ በላይ የጠቀስነው ለመሆኑ በጣም ግልጥ ነው፡፡

የአረብኛው ‹የሕፃንነት ወንጌል› በኋላ ወይንም ባልታወቁ ጊዜያት ከተጻፉት አፖክሪፋዊ ስራዎች አንዱ ሲሆን በማናቸውም ዓይነት የክርስትያን ቡድን ከእግዚአብሔር የመጣ ነው ተብሎ  ተቀባይነትን በፍፁም አግኝቶ አያውቅም፡፡ በቁርአን ውስጥ ምልክታቸውን ካስቀመጡት ሌሎች ተመሳሳይ ክፍሎች አንዱ ‹የእስራኤላዊው የቶማስ ወንጌል›፤ ‹የጀምስ ፕሮቶኢቫንጀልየም›፤ ‹የኒቆዲመስ ወንጌል› (አለበለዚያም ‹ጀስታ ፒላቲ› ተብሎ የሚጠራው) እና ‹የአርማቲያው ዮሴፍ ታሪክ› ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት እንደተመለከትነው ሁሉ መሐመድ ታማኝነት የሌላቸውን ምንጮች በማግኘት በኩል እጅግ አስደናቂ የሆነ ችሎታ ነበረው፣ ምክንያቱም የእውነተኛነት ምንጩ የማያጠራጥር አንድንም ጽሑፍ በፍፁም ጠቅሶ አያውቅም ነበርና፡፡ እነዚህና እነርሱንም የሚመስሏቸው ሌሎች መጽሐፍት በዚያን ጊዜና ኋላም በጣም ቆይቶ ምንም በማያውቁት ክርስትያኖች ዘንድ በጣም ታዋቂዎች የነበሩ ቢሆንም በማንም ላይ ጫናን ለመፍጠር የታቀዱ ነበር ለማለት አይቻልም፣ እነርሱም ለሁሉም ግልጥ የነበሩ የሃይማኖታዊ ድንቅ ነገሮች ብቻ እንደነበሩ ግልጥ ነው፡፡ እነርሱም በተፈጥሮ የሰዎችን ጉጉት በሚስቡ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኩሩ ነበረ፣ ስለዚህም የሚያነቡት ነገር እውነት መሆኑንና አለመሆኑን ምንም በማይጠይቁት ሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተው ነበር፡፡ አንባቢዎቻቸውም እነዚህ ታሪኮች ከጥንት ልማድ የመጡ ናቸው በማለት ለማመን ተስማምተው ነበር፤ ነገር ግን የቀኖና መጻሕፍት ጥቂት ወይንም ምንም በማይናገሩባቸው ነገሮች ላይ ነበር የሚያተኩሩት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለእነዚህ አፈታሪኮች ዋጋ ሰጥተዋቸው የነበረ መሆኑ ምንም ጥርጥር አልነበረውም ነገር ግን ማንም ትምህርት የቀመሰ ሰው እነዚህን የጠቀስናቸውን መጻሕፍት ዋጋ እንዳላቸው ተናግሮ አያውቅም፡፡ እነዚህም መጻሕፍት ቀኖናዊ ናቸውን ወይንስ አይደሉም በሚል ውዝግብ ውስጥ ከገቡት Antilegomena በመባል ከሚታወቁት መጻሕፍት ቡድን ውስጥ እንኳን አልተካተቱም ነበር፡፡ ምንም እንኳን እጅግ ብዙ ተረታዊ ተረቶች ተጨምረውባቸው ቢሆንም አንዳንዶቹም በጥንት ጊዜ ከጠፉት ስራዎች እንደገና የተቀናበሩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይህ እንዲህ ቢሆንም ወይንም ባይሆንም  እንዲሁም ምንም ስልጣን ባይኖራቸውም እንኳን አንዳንድ ጊዜ በጣም ጥንታዊ የሆኑ አፈታሪኮችን ብዙ ጊዜ አካተው ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በላይ በጥንታዊ ቡድሂዝም ውስጥ ያሉ የተረት ታሪኮችን አንዳንድ ማስረጃዎች እንደምናይባቸውም አይተናል፡፡ ለምሳሌም ያህል  ኢየሱስ በአንቀልባ ላይ ታዝሎ በነበረበት ጊዜ ለሰዎች የመናገሩ ታሪክ ተመሳሳይ ነው ምንም እንኳን ይህንን በፓሊ ቀኖና መጻሕፍት ውስጥ ለማግኘት ባይቻልም፡፡ በላሊታ ቪሰታራ፤ በቡድሃ ካሪታ፤ እንዲሁም በሌሎች የሳንስክሪት ስራዎች ውስጥ የዚያ ቀኖና ተረት የተነገረው ለቡድሃ ነው፡፡ ‹በፍቅር አፈታሪክ› ውስጥ እኛ በጥልቅ የተነገረን ነገር እርሱ ወዲያው እንደተወለደ፤ ቡድሃ ‹ወዲያውኑ ወደ አራቱም አቅጣጫ ሰባት እርምጃዎችን ወደፊት ተራመደ፣ እርሱም እየተራመድ በእያንዳንዱ እርምጃ ከእግሩ ስር የሎተስ አበባ ከምድር ውስጥ ብቅ አለ፡፡ በእያንዳንዱም አቅጣጫ ትኩር ብሎ ሲመለከት አንደበቱ እነዚህን ቃላቶች፡ ‹በዓለም ሁሉ ላይ እኔ ዋናው ነኝ› በማለት አፈለቀ፡፡ በሌላ የቻይና ሳንስክሪት ስራ ውስጥ ደግሞ ተመሳሳዩ ታሪክ ከሚከተለው የቡድሃ ቃላት ልዩነት ጋር ተነግሯል፡ ‹ይህ ልደት በቡድሃ ሁኔታ ላይ ነው፡ ከዚህ በኋላ እኔ በታደሰ መወለድ እጨርሳለሁ፣ አሁን ብቻ ነው ለአንድ ጊዜ የተወለድኩት፤ ይህም ዓለምን በሙሉ ለማዳን ዕቅድ ነው›፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር በእግዚአብሔር የለሹ የቡድሂዝም ስርዓትና በክርስትያኖች መካከል ያለውን ልዩነት መፍቀድ እንደሚያስፈልግ ነው፣ ይህ የመጨረሻው ጥቅስ ስለ ሕፃኑ ክርስቶስ በጠቀስነው ከአረብኛው ‹የሕፃንነት ወንጌል› ጋር አስደናቂ የሆነ ብዙ መመሳሰልን ይዟል፡፡ በእርግጥ የኋለኛው የመደምደሚያ ቃላት ከበፊቱ ጋር ቃል በቃል እንኳን አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ ጌታችን እንደታዘለ ተናግሯል የሚባለው እውነታ በሚከተሉት የቁርአን አንቀፅም ውስጥ ተረጋግጧል፡ ከሌሎቹ ነገሮች ጋር አብሮ አሁን እኛ እንደምንመለከተው ነው፡፡ ለመረዳት እንዲረዳንም የቁርአን 5.110 ከዚህ ቀጥሎ እንጠቅሰዋለን፡- ‹አላህ በሚል ጊዜ (አስታውስ) የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! በአንተና በእናትህ ላይ (የዋልኩላችሁን) ጸጋዬን አስታውስ በሕጻንነትና በከፈኒሳነት (የበሰለ ሰው ኾነህ) ሰዎችን የምትናገር ስትኾን በቅዱሱ መንፈስ (በገብርኤል) ባበረታሁህ ጊዜ ጽሕፈትንና ጥበብንም ተውራትንና ኢንጂልንም ባስተማርኩህ ጊዜ ከጭቃም የወፍ ቅርጽ ብጤ በፈቃዴ በምትሰራና በውስጧ በምትነፋ ጊዜ በፈቃዴም ወፍ በምትሆን ጊዜ ዕውርም ሆኖ የተወለደውንና ለምጻምንም በፈቃዴ በምታሽር ጊዜ ሙታንንም በፈቃዴ (ከመቃብራቸው) በምታወጣ ጊዜ የእስራኤልንም ልጆች በተአምራት በመጣህባቸውና ከነሱ እነዚያ የካዱት ይህ ግልጽ ድግምት እንጂ ሌላ አይደለም ባሉ ጊዜ (ሊገድሉህ ሲያስቡህ) ከአንተ ላይ በከለክልህም ጊዜ (ያደረግሁልህን ውለታ አስታውስ)› ቁርአን 5.110፡፡

በዚህ ቦታ ላይ የጌታችን ዓይነ ስውሩን የመፈወስ ተዓምር፣ የለምፃሙን ማንፃት እና የሙታንን ማስነሳት ተደርጎ እዚህ ላይ የተያያዘው ተዓምር ከአራቱ ቀኖናዊ ወንጌሎች በቀጥታ ተወስዶ ይሆናል፣ ምንም እንኳን ተመሳሳይ ክስተቶች ያልተወገዱ ቢሆንምና በአፖክሪፋ ወንጌሎች ውስጥ ሊሆኑ እንደማይችሉ ነው፡፡ ነገር ግን ለአሁኑ ዓላማችን ግን ዋናውና ጠቃሚው ነጥብ እርሱ ‹ከጭቃ የወፍን ቅርፅ ሰርቶ ሕይወትን ሰጠ› የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ክስተት የተወሰደው ‹ከእስራኤላዊው የቶማስ ወንጌል› ላይ ነው ይህንንም በሁለተኛው ምዕራፍ እንደሚከተለው እናነባለን፡-

‹ይህ ሕፃን፣ ኢየሱስ የአምስት ዓመት ሆኖት፣ በወንዝ ማቋረጫ ላይ ይጫወት ነበር እርሱም የሚፈሰውን ውሃ በአንድ ቦታ ላይ ያጠራቅምና ከዚያም በኋላ አጣርቶ ንፁህ ያደርግ ነበር እንዲሁም በአንድ ቃል ብቻ እነርሱን ያዛቸው ነበር፡፡ የተወሰኑ የሸክላ ጭቃዎችንም ካደቀቀ በኋላ ከእነርሱም ውስጥ አስራ ሁለት ድንቢጥ ወፎችን ሰራ፡፡ እነዚህን ነገሮች ይሰራ የነበረበትም ቀን ሰንበት ነበር ፡፡ ይሁን እንጂ ከእርሱ ጋር ይጫወቱ የነበሩ ብዙ ልጆችም አብረውት ነበሩ፡፡ ነገር ግን አንድ አይሁዊ ኢየሱስ ይሰራ የነበረውን ነገር እንዲሁም በሰንበት ቀን መጫወቱን አይቶ በቀጥታ ለአባቱ ለዮሴፍ በመሄድ ነገረው፣ እነሆ ልጅህ በወንዙ ዳር ነው ጭቃንም ወስዶ ከእርሱ አስራ ሁለት ድንቢጥ ወፎችን ሰራበት ሰንበትንም አርክሷል› አለው፡፡ ዮሴፍም ወደ ቦታው መጥቶና ተመልክቶ ወደ እርሱ በመጮኽ ‹በሰንበት ቀን ለማድረግ ያልተፈቀደውን ነገር ለምን አደረግህ?› አለው፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ እጆቹን በአንድ ላይ በማጨብጨብ ወደ ድንቢጦቹ ጮኸና እንዲህ አላቸው ‹ሂዱ!› ከዚያም ድንቢጦቹ እየተንጫጩና እየበረሩ ሄዱ፡፡ ነገር ግን አይሁዶቹ ይህንን አይተው፣ በጣም ተደነቁ ከዚያም ሄደው ኢየሱስ ሲያደርግ ያዩትን ሁሉ ለዋኖቻቸው ተናገሩ›፡፡

ይህ ተረት ሙሉውን በአረብኛው ‹የሕፃንነት ወንጌል› ውስጥ ሁለት ጊዜ ተጽፎ ይገኛል፣ አንደኛው በምዕራፍ 36 ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሌላ መንገድ በምዕራፍ 46 ውስጥ ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ የሁለተኛው የመጽሐፉ ክፍል የተወሰደው ከ‹እስራኤላዊው የቶማስ ወንጌል› ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡

እዚህም ላይ እንደገና የምንገነዘበው ነገር ከዚህ በላይ ያለው አፈታሪክ በቁርአን ውስጥ ከተነገረው ጋር አንድ ዓይነት ሆኖ እያለ ልዩነቱ በትክክል የሚያረጋግጠው ነገር ቢኖር መሐመድ ከሚያስታውሰው ውስጥ በአጭር መልክ እንዳስቀመጠው ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ መሐመድ ከሚያስታውሰው ሲናገር ምንም የተጻፈ መረጃን አለመጠቀሙን ለማስረዳት በቂ ነው፡፡ ስለዚህም አስራ ሁለት ወፎችን ከመጥቀስ ይልቅ እርሱ የጠቀሰው አንድ ወፍን ነው፣ እንዲሁም ለወፉ ሕይወት የተሰጠው በኢየሱስ ትዕዛዝ ከመሆኑ ይልቅ በትንፋሹ እንደሆነ ነው፡፡ በቁርአን ውስጥ የዚህ አጭር ታሪክ መኖር የሚያመለክተው ነገር በጊዜው ታሪኩ በጣም የተሰራጨና ታማኝነትም ያገኘ መሆኑን ነው፡፡ ይህም እንደገና የሚያረጋግጠው ነገር በመዲና ውስጥ በጣም ጥቂት የሆነ የአዲስ ኪዳን እውቀት እንደነበረ ነው፡፡ የዚህም ምክንየቱ በጌታችን የሕፃንነት በእርሱ ተደረጉ የተባሉ የተዓምራቶች ምንም ማስረጃ በቀኖናዊ ወንጌሎች ውስጥ ስለማናገኝ ሲሆን፤ ነገር ግን የዮሐንስ ወንጌል 2.11 ግን እርሱ ሠላሳ ዓመት ሆኖት እስከተጠመቀ ድረስ ምንም ተዓምራትን እንዳላደረገ ያመለክታልና፡፡

4. የማዕዱ ታሪክ

ይህ በክርስቶስ ተደርጓል ተብሎ የተጠቀሰው ተዓምር የሚገኘው በቁርአን 5.112-115 ውስጥ ሲሆን የምዕራፉም ስም የመጣው ከዚህ ነው፡፡ ከአማርኛው ቁርአን ላይ ያለው እንደሚከተለው ይነበባል፡-

‹ሐዋርያት፡- የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ ጌታህ በኛ ላይ ከሰማይ ማእድን ሊያወርድልን ይችላልን? ባሉ ጊዜ (አስታውስ) ምእመናን እንደሆናችሁ አላህን ፍሩ አላቸው፡፡ ከርሷ ልንበላ ልቦቻችንም ሊረኩ እውነት ልናውቅና በርሷም ላይ ከመስካሪዎች ልንኾን እንፈልጋለን አሉ፡፡ የመርየም ልጅ ዒሳ አለ፡- ጌታችን ሆይ ለኛ ለመጀመሪያዎቻችንና ለመጨረሻዎቻችን ባዕል (መደሰቻ) የምትኾንን ከአንተም ተአምር የሆነችን ማእድ ከሰማይ በኛ ላይ አውርድ ስጠንም አንተ ከሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነህና፡፡ አላህ፡ እኔ (ማእድዋን) በናንተ ላይ አውራጅ ነኝ በኋላም ከናንተ የሚክድ ሰው እኔ ከዓለማት አንድንም የማልቀጣውን ቅጣት እቀጣዋለሁ አለ፡፡››

ኢትዮጵያ ውስጥ በስደት የነበሩት ሙስሊሞች ይህንን የመሰለ አፈታሪክ ከኢትዮጵያ ይዘው ካልተመለሱ በስተቀር የዚህን ተረት ምንጭ ነው ለማለት የምንገደደው የአዲስ ኪዳን አንቀፆች የተሳሳተ መረዳት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አፈታሪክ በአንድ ቦታ ከተገኘ ግን እኛ እስካሁን ድረስ ያልደረስንበት ዋናው ምንጩ ከእርሱ ጋር የተያያዘ ነው ማለት ነው፡፡ የዚህ ጥቅስ መገኛ ሊሆን የሚችለው አንዱ የአዲስ ኪዳን ክፍል ሉቃስ 22.29-30 ነው፤ በዚያም ላይ  ጌታችን ኢየሱስ ለደቀመዛምርቱ የሚከተለውን ነገር አላቸው፡ ‹አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ።› መሐመድም ያለምንም ጥርጥር ክርስትያኖች በማቴዎስ 26.20-29 በማርቆስ 14.17-25 በሉቃስ 22.14-30 በዮሐንስ 13.1-30 እና በ1 ቆሮንቶስ 11.20-34 መሠረት የጌታን እራት እንደሚያከብሩ ያውቃል፡፡ ነገር ግን ከሰማይ የወረደው ማዕድን ሐሳብ የመራው ነገር ሐዋርያት ስራ 10.9-16 ላይ ያለው ክፍል እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፣ በዚያም የሚከለተውን ከጴጥሮስ ጋር የተያያዘውን ክስተት እናነባለን፡

‹እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ። ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት። ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን። ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና አለ። ደግሞም ሁለተኛ። እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ።›

ከቁርአን 5 ላይ የጠቀስናቸው የአንቀፁ የማቃለያው ቃሎች መሐመድ ስለጌታ እራት እያሰበ የነበረ ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃዎች ናቸው፣ ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ፡ ‹ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና።› 1ቆሮንቶስ 11.27-29 ላይ ለሰጠው ማስጠንቀቂያ ቀጭን ማስተጋባት ይመስላሉና፡፡  

አጠቃላይ አንቀፁ መሐመድ የአዲስ ኪዳን በጣም ትንሽ እውቀት ብቻ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ መጽሐፉን ያነበበ ወይንም የሰማ ማንም ቢኖር የጴጥሮስን ራዕይ ከጌታ እራት ምስረታ ጋር አያይዘውም ወይንም ያንን ራዕይ በጌታችን የምድር ዘመን የወደፊት ራቅ ያለ ጊዜ ሊሰጥ በሚችል የማዕድ ገበታ አይለውጠውም፡፡ ይህ አንቀፅ አፈታሪኮች እንዴት እንደሚነሱና እንደሚያድጉ የሚያሳይ አስደናቂ ምሳሌ ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡

በቁርአን ውስጥ ያለው የጌታ ኢየሱስ ታሪክ ምንጭ ከየት እንደመጣ ከዚህ በላይ ያለው ጽሑፍ ግልፅ አድርጎልናል፡፡ ይህ በጣም አስደናቂ እውነት ሙስሊም አንባቢዎች የሚከተሉትን እምነት ምንነት ቆም በማለት እንዲያስቡ ሊረዳቸው ይችላል፡፡ ስለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ መረጃ የሚገኘው መሐመድ በቁርአን ውስጥ ‹... ኢንጅልንም በውስጡ ቀጥታና ብርሃን ያለበት በስተፊቱ ያለችውን ተውራትንም የሚያረጋግጥ ለጥንቁቆችም መሪና ገሣጭ ሲኾን ሰጠነው› (ቁርአን 5.46) ብሎ በተናገረለት በወንጌል መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ያለው ጽሑፍ ያረጋገጠው መሐመድ ወንጌልን የማንበብ ዕድል እንዳላገኘ ነገር ግን በዘመኑ ይዘዋወሩ ከነበሩ የውሸት ወንጌሎች ጋር ግንኙነት እንደነበረው ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንባቢ ስለ እውነተኛ ወንጌልና በውስጡ ስላለው መልእክት ለማወቅ መናፈቅ ይኖርበታል፡፡ ወንጌል ምንድነው በውስጡስ ያለው መልእክት ምንድነው ጠቃሚ ነውን የሚያስረዳውስ መልእክት ወጥነት ይኖረዋልን? የሚሉትን እራሱ እንዲገነዘብ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያገኝና እንዲያነብ እናበረታታዋለን፡፡

እውነተኛው ወንጌል የያዘው መልእክት አስገራሚና ያልተለወጠ ነው፡፡ ወንጌል ስለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ለምን ሰው መሆን እንዳስፈለገው ይገልፃል፡፡ ከዚያም ጌታ ኢየሱስ ስለምን ለእኛ ለሰው ልጆች መሞት እንደተገባው ያስረዳል፡፡ ወንጌልን ስናነብ ታላቁ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን አስደናቂ ፍቅር እናስተውላለን፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የሰው ልጅ በኃጢአቱ ምን ያህል ከፈጣሪው እሩቅ እንደሆነና የዘላለም የሲዖል ፍርድ በላዩ ላይ እንዳለበትም ጭምር እናስተውላለን፡፡

የሰው ልጅ ከሚወደው ፈጣሪ በኃጢአቱ ከመራቁና በፃድቁ እግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ ከሆነ እንዴት ሊድን እና ከፈጣሪው ጋር ሊታረቅ ይችላል? ወንጌል ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቂያውን መንገድ የምስራች ዜና አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ግሩም ዜና ነው አንብቡት እጅግ በጣም አስደናቂ ተስፋንና የዘላለም ሕይወትን በነፃ ስለማግኘት እርግጠኛ የምትሆኑበት መንገድ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት እንደተከፈተ ያሳያችኋል፡፡ እግዚአብሔር በፀጋውና በምህረቱ ይህንን እውነት እንድታስተውሉ ይርዳችሁ፡፡

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ