እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ

[ክፍል አንድ] ክፍል ሁለት [ክፍል ሦስት]
ቅንብር በአዘጋጁ

 

ሁለቱ እስላማዊ ርዕዮተ ዓለሞችና ትግላቸው

በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ፣ ለመደገፍ፣ ወይንም ዝም ብሎ ለማየት ወይንም ለመቃወም የሚቻለው እስልምና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምን ይመስል እንደበረ በትክክል በመገንዘብ ነው፡፡ የአሁኑ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በእርግጥ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ነውን? ብዙዎችን መስሏቸዋል፡፡ በጣም የቅርቡ በኢትዮ ሚዲያ የድረ-ገፅ ጽሑፎች ላይ የቀረበው የኦክላንድ መግለጫ www.ethiomedia.com/2012_report/auckland_muslim_affairs.pdf August 12, 2012, እንዲሁም በዚያው ኢትዮ ሚዲያ በJuly 14th 2012  www.ethiomedia.com/2012_report/4059.html የቀረበው የነጃሺ ካውንስል መግለጫ፣ አሜሪካ ውስጥ ባለው በኢትዮጵያ ክርስትያንና እስላም ካውንስል በJuly 26 2012 በኢትዮ ሚዲያ ላይ የወጣው www.ethiomedia.com/2012_report/4097.html ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሁም በሌሎች ድረገፆች ላይ በተደጋጋሚ የተሰጡት መግለጫዎች በሙሉ ሁኔታውን ያቀረቡት የእምነት ነፃነት ተደፈረ ከሚል አመለካከት የተነሳ ነው፡፡

ይህንን በተመለከተ የሚጻፉትም የተለያዩ ጽሑፎች አስገራሚዎች ሆነው አግኝተናቸዋል፤ በተለይም በዚያው በኢትዮ ሚዲያ ላይ Standing up with our Moslem citizens በሚል ርዕስ በይልማ በቀለ የቀረበው ጽሑፍ ለምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ሙሉ ጽሑፉን www.ethiomedia.com/2012_report/4554.html ማንበብ ይቻላል፡፡ አቶ ይልማ በቀለ የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ እንደ እውነተኛ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ አቅርቦ የገዚው ፓርቲ እነርሱን ለማፈን አንዳንድ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳዎችን እንደተጠቀመ በማድረግ አስቀምጦታል፡፡ በእርግጥ ይልማ በቀለ እንዳለው ኢትዮጵያን የምንመኛት የሁሉም እምነት ተከታዮች በነፃነት የሚኖሩባት አገር እንድትሆን ነው፡፡ የሙስሊሞች ጥያቄና የዘመናት ዕቅድ ግን በእርሱና በመሰሎቹ ዘንድ የታየው ላይ ላዩን ከሚሆነው ነገርና  ከሞኝነትም ጭምር የተነሳ ነው ምክንያቱም ነገሩ ሁሉ እነሱ እንደሚሉት አይደለም፡፡

ሙስሊሞች በተለይም በአሁኑ ተቃውሞ ውስጥ የተሳተፉት መሰረታዊ ፍላጎታቸው በእርግጥ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ነውን? የአንድ አገር መንግስትስ  በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ለመግባታ ስለምን ይገደዳል? በስልጣን ላይ ያለ አንድ መንግስት በሃይማኖት ስም የተቀነባበረና አገሪቱን ችግር ውስጥ የሚጥል አደጋ ሲመጣ እያየና መረጃዎችና ማስረጃዎች እያለውና እያወቀ ዝም ሊልስ ይገባዋል ወይ? ለዚህ ነው የተሰጡት መግለጫዎች እና ይልማ በቀለን በመሳሰሉ ሰዎች የቀረቡት ጽሑፎች ሚዛን የጎደላቸውና ታሪካዊ ምንጮችን ያላገናዘቡ የሆኑት፡፡

የዚህ ድረገፅ አዘጋጆች ካለው ውዥንብርና መወናበድ ባሻገር ያሉትን ታሪካዊ ምርምሮችን እና አቅጣጫ ጠቋሚ እውነታዎችን ማሳየት የተገደዱት ለዚህ ነው፡፡ ከገዢው ፓርቲ መርሆ የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት በእርግጥ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ጋዜጠኞች በእስር ላይ የሚገኙት፡፡ ሰዎች የፈለጉትን እምነት የመከተልም ነፃነት በመጠኑ የለም ማለት ይቻላል፣ ይሁን እንጂ የአሁኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ መሰረታዊው ጥያቄ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም የሃይማኖት ነፃነት አልተነፈጋቸውምና፡፡ እንዲያውም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሙስሊሞች ነፃነት ያገኙት በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ስር መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ታዲያ ለሙስሊሞች እንቅስቃሴ መሠረታዊው ምክንያት ምንድነው?

እነዚህንና ከዚህ ጋራ ተያይዘው የሚመጡ ጥያቄዎችን ለመመለስ የምንችለውና ትክክልም አቋም ላይ የምንደርሰው የእስልምናን እምነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምን ይመስል እንደነበረ ስናየው ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አስፈላጊና ዓይን ከፋች ሆኖ ያገኘነው የፕሮፌሰር ኤርሊችን እና የፕሮፌሰር ካብሃን የምርምር ጆርናል ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱም ቢያንስ አሁን በምናየው ጆርናል ላይ የሌላ አገር ተወላጆችና የታሪክ ተመራማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካም ሆነ ሃይማኖት ውስጥ የተለየና ወደ አንድ አቅጣጫ ያዘመመ አመለካከት የላቸውም፡፡ ስለዚህም የእነርሱን ስራ ማየት ሚዛናዊ አመለካከት ላይ እንድመጣ ይረዳናል፡፡ በመሆኑም ይህንን ክፍል ሁለት ጽሑፍ እናቀርባለን፡፡

የአል-አሕበሽ እድገት፡

ፕሮፌሰሮቹ ስለ አል-አሕባሽ ርዕዮተ ዓለም መስራች ስለ ኢትዮጵያዊው ሼክ አብደላ እንደ ጻፉት፡ በ1983 ወደ እይታ ብቅ እንዳለና እንደ ታዋቂ ፈላስፋ እንዲሁም ጸሐፊ ዝናን እንዳገኘ፣ ቀጥሎም ወደ ሃያ መጽሐፍትንም እንዳሳተመ ከዚህም የተነሳ ሙፍቲ፣ እና ሰባኪም ሆኖ ዝናን እንዳገኘ አቅርበዋል፡፡ የዚህ ሰው ርዕዮተ ዓለማዊው መልእክት ምንድነው?

የእርሱም ዋና መልእክት ሆኖ የቀረበውና የሚሟገትለት ርዕዮተ ዓለም ከኢትዮጵያ ያመጣው ትምህርት ነው፡፡ የእርሱ ትምህርት በሊባኖስም ውስጥ በማዕከላዊነት በጣም ጠቃሚ ሆኖ እንደነበርና መልእክቱም፡ “እስላምና ክርስትያን አብረው በሰላም ይኖራሉ” የሚለው እንደነበር የታሪክ ሊቃውንቱ ይናገራሉ፡፡ ወዲያውም እርሱ ከብዙ እስላማዊ ማህበሮችና በተዘዋዋሪም ከሊባኖስ ክርስትያናዊ ድርጅቶችም እንኳን እርዳታዎችን አግኝቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር እርሱ የማህበሩ መሪ የመሆኑ ጉዳይ ሶርያ ሊባኖስን ከመውሰዷ ጋር ተገጣጥሞ እንደነበር ታሪክን ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡

ቀጥለውም ያስቀመጡት ነጥብ አዲሶቹም የሶርያ ባለስልጣናት ለያዙት የሴኩላር አረብ ባዝ ዶክትሪን የኢትዮጵያዊው ሼክ “እስላማዊ ክርስትያን” መልእክት ከእነርሱ አቀራረብ ጋር አብሮ የሚሄድ ሆኖ አግኝተወታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማህበሩ በጣም በገነነ መልኩ የሚታወቀው “አል-አሕበሽ” ተብሎ ሲሆን በሊባኖስ ፖለቲካም ውስጥ ዘው ብሎ የመግባት ዕድልን አግኝቷል ይላሉ፡፡ ስለዚህም የድርጅቱ አባል ዶ/ር አድናን አል-ታባቡልሲ በ1989 በሊባኖስ ፓርላማም ውስጥ መቀመጫን እንዳገኘ ያስረዳሉ፡፡ የሼኩ ድርጅት አል-አሕበሽ፤ ለሶርያ ባዝ ፓርቲና በሊባኖስ ውስጥ ላሉት የእርሱ ተባባሪዎች፣ ለክርስትያኑ የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ኢልያስ አል-ሃዋሪ (1989-1998) እና ለእርሱ ተከታይ ኢሚል ላሁድ (1998 -) እንዲሁም ለሙስሊሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳሊም አል-ሑስና ራፊክ አል-ሃራሪ ያበረከተው የማያጠራጥር ትብብር በመንግስታዊ እርዳታ ደረጃ ሽልማትን አስገኝቶለት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

የአል-አሕበሽ ማህበር በሊባኖስ ውስጥ ከፍተኛ ዕድገትን አግኝቷል፡፡ ማህበሩ ወርሃዊ የሆነ ማኑር አል-ሁዳ የሚባልን ጋዜጣ ከ1992 ጅምሮ ሲያወጣ ቆይቷል እንዲሁም ከ1998 ጀምሮ ኒዳ አል-ማሪፋህ የተባለ የራሱ የሆነ የራዲዮ ጣቢያ እንዳለው፡፡ አባላቶቹ በኢንተርኔት ላይ እጅግ በጣም በትጋት እንደሚሰሩ በመሆኑም የሼኩን ቃልና እርሱ በተቃራኒዎቹ ላይ የሚያስተላልፈውን ትምህርት እንደሚያሰራጩ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማህበሩ የልጆች ትምህርት ኔት ወርክን  የኤለመንታሪና የሰከንደሪ ትምህርት ቤቶችንም እንዲሁም ከካይሮው ጃሚያት አል-አዛር ጋር የተቀራረበ እስላማዊ ኮሌጆችን  ጭምር እንደሚያካሂድ በምርምር ስራዎቻቸው ላይ አቅርበዋል፡፡

የአል-አሕበሽ መልክእትም ሁልጊዜ ጊዜ በግልጥነት ስለሚሰራጭና እንዲሁም ማህበሩ በሊባኖስ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ያለው አስተዋፅዖ ህልውናና ያገኘው ጥሩ ስሜት ብዙውን ጊዜ በሳላፊዎችና በዋሃቢዎች አካባቢ ተቃውሞንና ጥላቻን እንደቀሰቀሰበት የታሪክ ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ ከ1980ዎቹ ጀምሮ መጠነኛ የሆኑ ግጭቶችና የጎዳና ላይ ሽብሮች ታይተው እንደነበርና እነዚህም ግጭቶች በ1995 ከፍተኛ ጣሪያ ላይ ደርሰው በቤይሩት የማህበሩ መሪ ኒዛር ሃላቢ ተገድሏል፡፡ ይህም ክስተት በ“ኢትዮጵያውያኖቹ” ማለትም በአል-አሕባሾቹና እና በዋሃቢያዎቹ መካከል ያለውን ጥላቻ (ጠላትነት) ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው የታሪኩ ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የሊባኖስ ዲያስፖራ አል-አሕበሽን ዓለም አቀፍ ማህበር እንዲሆን በ1980 እረድተውታል፡፡ የድርጅቱም ዓለም አቀፍ ማዕከል ያለው በዩሮፕ በጀርመን ውስጥ ሲሆን በጣም ትጋት ያላቸው ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ በምዕራብ ዩሮፕ ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዳላቸው ምሁራኑ ይጠቁማሉ፡፡ ይህ አል-አሕበሽ በኢንዶኔዥያ በማሌዢያ በፓኪስታን በጆርዳን በግብፅ በአውስትራሊያ እና በአሜሪካ የሚንቀሳቀሱም ቅርንጫፎች አሉት፡፡ አል-አሕበሾች በአፍሪካም ውስጥ በጣም ንቁ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ (በናይጀሪያ እና በጋና በጣም በከፍተኛ ደረጃ) ከዚህም የተነሳ በአካባቢያዊ ሙስሊሞችና በመካከለኛው ምስራቅ ማዕከላዊዎች መካከል ድልድይን ለመስራት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡ በ1990ዎቹ ላይም አል-አሕበሽ እስላማዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ ሁሉ የሚገኝና ዓለም አቀፍ የሆነ እንዲሁም በጣም በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ እስላማዊ ድርጅት ለመሆን በቅቶ እንደነበርና በዚያን ጊዜ ብቻ ሩብ ሚሊየን ያህል አባላት እንደነበሩት የነፕሮፌሰር ኤርሊች ጆርናል ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያውያን በአል-አሕበሽ ውስጥ፡

ይሁን እንጂ በአል-አሕባሽ ድርጅት ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያውያን አባላት ቁጥር አይታወቅም፣ በማለት የሚናገረው ጆርናል ጉዳዩን የደመደመው በውስጡ ያሉት ኢትዮጵያውያን፤ “ነገር ግን ብዙ አይደሉም” በማለት ነው፡፡ ከሐረር ከሆነው ከሼክ በስተቀር የእንቅስቃሴው አጠቃላይ አባላት ከተለያዩ ሌሎች አገሮችና ቋንቋ የተውጣጡ ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱም እራሳቸውን የሚጠሩት “ኢትዮጵያውያኖች” በማለት እንደሆነና ይህንንም ያደረጉት በከፊል ለመሪያቸው ስላላቸው አድናቆትም ጭምር እንደሆነ የታሪክ ሊቃውንቱ ያስረዳሉ፡፡ የአል-አሕበሽ ተከታዮች ሼክ አብደላን የሚያዩት ከእስላም ሊቃውንት መካከል አንዱና ታላቁ ሊቅ እንደሆነ አድርገው ነው፡፡ ከዚህም በላይ የሚከተለውን የማዕረግ የመጠሪያ ስምን በመጠቀም እንደሚጠሩት  ጠቁመዋል፤ “አል-ኢማን አል-ሙሃዲት” ወይንም “ሙሃዲት አል-አሳር”፣ ትርጓሜውም “የሐዲት ሊቃውንት መሪ” እንዲሁም “የጊዜያችን የሐዲት ሊቅ” ማለት እንደሆነም አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህም በላይ እርሱ የሚጠራው እንደ አል-ሃፊዝ ተብሎም ነው፤ ትርጉሙም የጥበብና የሊቅነት ጠባቂ ማለት ነው፡፡

ፕሮፌሰሮቹ እንደሚሉት ሼኩ እራሱ አረባዊ ጀርባ አለው ተብሎ የሚነገረውን ነገር እንደሚኮራበትና፤ የእራሱም ሙሉ ስም “አብደላ ኢብን ሙሐመድ ኢብን ዩሱፍ አል-ሐራሪ አል-ሻይቢ አል-አብዳሪ” ይህም የኩራይሽ ዘር ያለው መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ አስቀምጠዋል፡፡ እርሱ ግን አረባዊነትን የሚቆጥረው እንደ ቅዱስ መለያና በሙስሊሞችና በክርስትያኖች መካከል የሚኖር ትክክለኛ ድልድይ አድርጎ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን በኢትዮጵያዊነቱም ሙሉ ትምክህት ወይንም ኩራትም አለው (ወደ ኢትዮጵያም ሁለት ጊዜ ተመልሶ ነበር በ1969 እና በ1995፣ በወቅቱም በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በጣም በከፍተኛ አክብሮትና ተቀባይነትን አግኝቶ ነበር) ይላሉ፡፡

የእርሱም ዓለም አቀፍ ብዙ ተከታዮች እራሳቸውን የሚያስቀምጡት ኢትዮጵያ ታሳየዋለች ደግሞም ምሳሌ ሆናበታለች ለሚሉት ለለዘብተኛና የመቻቻል ሙስሊምነት ትክክለኛነት መሆኑን ጆርናሉ ያስረዳል፡፡ ለዚህም ነው ይላሉ የሼክ አብደላ ተከታዮች እራሳቸውን አል-አሕበሽ በማለት የሚጠሩት ይህም ለዘብተኛ የሆነን እስልምና በመደገፍ ተስፋ ላይ የመመስረት ፍላጎት ነው፣ መልእክታቸውም ከክርስትያን “ሌላ” ጋር ሙስሊም አብሮ መኖር ይቻላል የሚል ነው፡፡

መሰረታዊና ታሪካዊ ጥያቄ፡

የሼክ አብደላ ርዕዮተ ዓለም በሌላው ዓለም ውስጥ ተቀባይነት ሲያገኝና ዓለም አቀፍ ሲሆን በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዘንድ  ተቀባይነት ስለምን ሊያገኝ አልቻለም? ይህ ጥያቄ በኢትዮጵያውያን መካከል መነሳትና መብላላት ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሁሉ ሊጠየቁበት የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄው በምንም መልኩ ቢላመጥና ቢገላበጥ የሚሰጠው መልስ ከሚከተሉት ከሁለቱ መልሶች መካከል ከአንዱ በፍፁም ሊዘል አይችልም፡

አንደኛ፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የእስልምና እምነት በጣም ጥንታዊ ወይንም የተለምዶ ብቻ ስለሆነ ነው፡ አል-አሕበሽን አይቀበልም፤ ወይንም፤

ሁለተኛ፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ስር የሰደደውና ብዙዎች የሚከተሉት የእስልምና እምነት ርዕዮተ ዓለም የዋሃቢው አክራሪ እስልምና ስለሆነ የአል-አሕበሽን ትምህርት አይቀበልም የሚሉት ብቻ ናቸው፡፡

እንግዲህ በአሁኑ ጊዜ የተነሳው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በማነው የተነሳው፣ ማን መራው፣ ዓላማው እና የወደፊት ግቡ ምንድነው የሚሉት ሁሉ መልሳቸውን የሚያገኙት ከዚህ መሰረታዊና ታሪካዊ ጥያቄ ጋር ተያይዘው ሲታዩ ብቻ ነው፡፡ ይህ ነጥብ ነው ለምናደርገው ነገርና ለምንሰጠው ድጋፍ ጥንቃቄ እንድናደርግ የሚጠራን፤ ይህ ነጥብ ነው ዛሬ ተቀምጠን የሰቀልነው ነገ ቆመን የማናወርደው እንዳይሆን የሚመክረን፣ ይህ ነጥብ ነው የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚለውን አባባል አቁመን አሁን አርቀን ለማሰብ መነሳት አለብን የሚለን፡፡

የአል-አሕበሽ መሰረታዊ እምነቶች

የአል-አሕበሽ መሪ ሼክ አብደላ ለተከታዮቹ ካደረጋቸው ንግግሮች ውስጥ በአንዱ እንቅስቃሴው የሚከተለውን መሰረታዊ ርዕዮተ ዓለም ለማስቀመጥ እንደሞከረና በዚያም ውስጥ ከዋነኛው ተቃዋሚ እራሱን ለይቶ እንዳስቀመጠ ፕሮፌሰሮቹ አመልክተዋል ንግግሩም፡-
 
“እኛ እስላማዊ ማህበር ነን፣ (ማህበራችን) የሚወክለውም ምንም ዓይነት የፈጠራ ልዩነት የሌለበትን ነው፣ ማለትም እንደነዚያ ከሃምሳ፣ ሁለት መቶ ወይንም ስድስት መቶ ዓመታት በፊት እንደተጨመሩት ዓይነት አይደለንም፡፡ የመጀመሪያዎቹ የሳይድ ካታብ ሐሳቦች ናቸው ... ሁለተኛዎቹ ደግሞ የመሐመድ ኢብን አብድ አል-ዋሃብ ናቸው፣ ሦስተኛዎቹ ደግሞ  የኢብን ታይሚያ ናቸው ከእነዚህ ነው አብድ አል-ዋሃብ ሐሰቦቹን ያመጣቸው፡፡ (የወሰዳቸው)፡፡ እኛ ግን አሻሪስ እና ሻፊዎች ነን፡፡ የእምነታችንም መሰረት አሻሪያ ሲሆን ሻፊያ ደግሞ የየዕለቱ መለያችን ነው፡፡” የሚል ነበር፡፡

በንግግሩ ውስጥ የጠቀሳቸውን ሰዎች እንደ ዋነኛ ጠላቶች አድርጎ ለምን እንደመረጣቸው እና ምክንያቱንም ሊቃውቱ ሲያስረዱ የሚከተሉትን ከታሪክ አቅርበዋል፡ ሳይድ ኩታብ የግብፅ እንቅስቃሴ መሪና ሊቅ ሲሆን፣ በእስልምና የፖለቲካል ሐሳቦች ላይ ሥራን በመስራት በሙስሊም ወንድማማችነትና በዋሃቢዝምን መሰረታዊ ነጥቦች መካከል ድልድይ የሰራውን መጥቀሱ እንደሆነ፡፡ ሼኩ አል-ዋሃብን እና ኢብን ታይሚያምን ሲጠቅስ ደግሞ የዋሃቢዝም መስራችና የትምህርቱ ታሪካዊ አነሳሽንና ምንጭን ማለትም ግልፅ የሆነውን ነገር ማንሳቱ ነበር ይላሉ፡፡ ኢብን ታይሚያ የ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሊቅ ነበር፡፡ ዘመናዊው የፓኪስታን ፈላስፋ አቡ አል-አላ አል-ማውዱዲ የተነሳሳው በኢብን ታይሚያ እና በሳይድ ኩታብ በተሰጠው በዋሃቢያ ትምህርት ነው፣ እርሱም የሙስሊም ወንድማማቾችን የሃይማኖታዊ ሕጋዊነት በመስጠት ከ1960 ጀምሮ ወደ አክራሪ እንቅስቃሴነት የመቀየር ህጋዊነት አምጥቷል ይህም እስላማዊ ያልሆኑትን እና መሰረታዊ ያልሆኑትን ትምህርቶችና ነገሮች በማስወገድ እስልምናን ለማጥራት ተብሎ ነበር፡፡ የአል-አሕበሽ መሪ እነዚህን አስተማሪዎችና መሪዎች ከታሪካዊ አስተምህሮአቸው በመነሳት የጠቀሰበት ዋናው ምክንያት እዚህ ላይ ግልፅ ነው፣ እርሱም እነርሱ በሙሉ ያራምዱት የነበረው እስልምና ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር የሚፈልግም የሚችልም እንዳይደለ ነው፡፡

የአል-አሕባሽን ስነ-ጽሑፎችን ሁሉ ማጥናት የሚያመለክተው ነገር የእነርሱን እስላማዊ የእራስ መለያ የሆኑትን አራት መሰረታዊ ነገሮችን እንደሆነ ፕሮፌሰሮቹ አስቀምጠዋል፤ እነዚህም፡ 

አንዱ ሕጋዊ የሆነው የእነርሱ የሻፊ ትምህርት ቤት ነው፡፡ የእነርሱም መሰረታዊ ርዕዮተ ዓለም የሚገኘው የአሻሪያ ስነ መለኮታዊ ቅርስ ውስጥ ሲሆን በውስጡም አንዳንድ የሱፊ ቃላቶች ይገኙበታል፡፡ በእነርሱም ክርክር ውስጥ የወከሉት አህል አል-ሱና ዋል-ጃማዓን ነው ማለትም የኦርቶዶክስ እስላማዊ እምነት ማህበረሰብን ነው ይህም በሱኒ እስልምና ማዕከላዊ አካሄድ ስምምነት ያለው ነው፡፡ ይህ ጥንቅር በራሱ የቲዎሎጂካል አዲስ ግኝት አይደለም እናም በብዙ መንገዶች አል-አሕበሽ የሚከተለው የመካከለኛው ዘመንን ታላቅ ፈላስፋ (ሊቅን) አቡ ሃሚድ አል-ጋዛሊን (1058-1111) አጠቃላይ አቀራረብን ነው፡፡

የሱፊው መሰረታዊ ሃሰብ ደግሞ በጣም ግልጥ ነው፡፡ ማህበሩ ከሦስት ታሪኮች ጋር የተያያዘ ነው፡ አንደኛው ሪፋይያዎች፣ ሁለተኛው ደግሞ ናክሻባንዲያዎች እና ሦስተኛው ካዲሪያዎች ናቸው፡፡ በሕትመቶቹ ውስጥና በሼኩ ስራዎች ውስጥ የሱፊ ቃላት በድግግሞሽ ይገኛሉ ለምሳሌም ያህል “የእርግጠኝነት ብርሃን” (ኑር አል-ኪን) ወይንም የእግዚአብሔር ፍቅር (እና የእርሱ ፍጥረት) (አል-ማሃባ ሊ-አላህ)፡፡ ሼኩ ምንም አጠያያቂ ባልሆነ መንገድ ከሐረር-ኢትዮጵያ መነሻው (ሐረር፣ ማዲናት አል-አወሊያ የቅዱሳን ከተማ ሁልጊዜ የሱፊዝም ዋነኛ ማዕከል ነው የሆነው) በታዋቂው እስልምና ውስጥም የራሱ ስር አለው በተለይም ደግሞ በሱፊዝም ማህበራዊ መልእክት ውስጥ፣ በባህል ጉዳዮች ውስጥ እንዲሁም የተነቃቁ እንቅስቃሴዎችን በማነሳሳትና በማንቀሳቀስ (ለመምራት)፡፡ እርሱም ወደ ቅዱሳን ሰዎች መቃብር ቦታ ሃጂ ማድረግን ማለትም ዚያራን በሱፊዝም ዋና ምሰሶ የሆነውን አምጥቷል ይህም እግዚአብሔር ጋ ለመድረስ መሰረታዊ መንገድ የሚለውን በእነርሱ ማማለድ በኩል (ታዋሱል) እንደሆነ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ የሱፊ መሰረታዊ ሐሳቦች ማዕከላዊዎች አይደሉም፡፡ የአል-አሕባሽ ትኩረቱ ወይንም አፅንዖት የሚሰጠው ሚስቲሲዝምን አይደለም፡፡ (ማለትም ከመናፍስት ጋር ይደረጋል የሚባለውን ቀጥታ ግንኙነት)፡፡ ሆኖም ግን ለአንዳንዶች ይምሰላቸው እንጂ የአል-አሕበሽ መለያ ሱፊዝም አይደለም በማለት የታሪክ ሊቃውንቱ እነ ፕሮፌሰር ኤርሊች ያስረዳሉ፡፡

ስለዚህም የእነርሱ ማዕከላዊ ርዕዮተ ዓለም የሻፊያ ሕጋዊነት ወይንም ደግሞ በሱፊዝም ሚስቲሲዝም ላይ አይደለም፣ ነገር ግን በአሻሪያ የሃይማኖት መርሆዎች ላይ ነው ይላሉ፡፡ የጥንቱ ሊቅ አቡ አል-ሃሳን አል-አሻሪ (ባስራ ኢራቅ ተወልዶ በባግዳድ የሞተው 874-936) በቅድሚያ እርሱ የሙታዚላ ፍልስፍና ትምህርት ቤት ተከታይ ነበር እርሱም እስልምናን በዲያሌክቲካል አስተሳሰብ ላይ ለመመስረት ይመኝ ነበር፣ የእርሱም አስተሳሰብ በከፊል ከግሪክ ፍልስፍና በብድር የተወሰደ ነው፡፡ የሙታሊዛ ተከታዮች በጊዜያቸው የዋናው የሱኒ ኦርቶዶክሲ እምነት ቀንደኛ ጠላቶች ነበሩ፣ እነርሱም ለቁራናዊ ክፍሎች የሚሰጡትን እንደዚህ ዓይነትን ትርጉሞችንና እንደዚህ ዓይነትን ሃይማኖታዊ አመለካከትን አይቀበሉም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጊዜው አል-አሻሪዎቹ ወደ ግማሽ መንገድ ፈቀቅ ብለው በመጠጋት የማመቻመችንና የዘመናዊነትን መካከለኛነትን መስበክ ጀምረው እንደነበር ጆርናሉ ያሳያል፡፡

በመሆኑም እርሱ የመሰረተው የእስላማዊ የመቻቻል መንገድ ብዙ መከፋፈሎችን ማቆም ችሎ እንደነበር በሱኒዎቹ ዓለም ውስጥ እንደ ድልድይ የሚያገለግል አቀራራቢ በመሆን አስተዋፅዖ እንደሰጠ ሊቃውንቱ አስቀምጠዋል፡፡  በሼክ አብደላ ዓይኖች መሰረት፣ አል-አሻሪ “የአህል አል-ሱና ዋላ-ጃማ” ኢማም ነበር”፡፡ ምንም እንኳን አል-አሻሪ ምንም ሕጋዊ ትምህርት ቤትን ባይመሰርትም ለሼክ አብደላ ግን እርሱ እንደ አምስተኛው የማድሃብ ማለትም የመቻቻልና የማመቻመች ትምህርት ቤትን መስራች ነበር፡፡ የሼኩ ተከታዮች የእርሱን አጠቃላይ አቀራረብ ተርጉመውታል ይህንንም ያደረጉት አስራ ሁለት ግብ ባላቸው መሰረታዊ ሓሰቦች ነው፡ ከእነርሱም ውስጥ በፕሮፌሰሮቹ የተጠቀሱት የሚከተሉት አምስቱ ብቻ ናቸው፡

1. ትክክለኛውን ሃይማኖት ማስፋፋት አህል አል-ሱና ዋል-ጃማ እናም ይህንን በጨዋነትና በጥበብ መንገድ ማድረግ፡፡

2.  በመጠን መሆንን ኢቲዳልን መስበክ እንዲሁም መልካም ባህርይን የሃይማኖት መርሆዎችን ተግባራዊ እንደማድረጊያ መንገድ መከተል ይህንንም ለማድረግ አክራሪነትንና ቅናትን በመዋጋት ላይ መሆን፡፡

5. ዘመናዊ ትምህርትንና ዓለም አቀፋዊ ተግባራዊ ሳይንሶችን ማስፋፋት ይህም  የትምህርት ቤቶች ተቋማትንና ዩኒቨርሲቲዎችን በማቋቋም፡፡

8. ለእናት አገር እና ለዜጎቿ ጥቅም በመግባባት መስራት እንዲሁም ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት እንዲሁም አካላት ጋር የሚገነባ ግልፅነት እና ፍሬያማ በሆነ ትብብር ማድረግ፡፡

12. የሴቶችን ጉዳይ በጥንቃቄ መያዝ እንዲሁም የእነርሱንም የተባበረ እንቅስቃሴ መደገፍ እንዲሁም ችሎታ ያላቸውን ሴቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ውስጥ እንዲሳተፉና እንዲተባበሩ መስራት፡፡ 

በድርጅቱ በተዘጋጁ ብዙ ጽሑፎች ውስጥና በሼኩ ንግግር ውስጥ ያለው ቁልፍ ቃል “ኢ-ቲዳል” መጠነኛነት ነው፡፡ ዋናውም ሃሳብ አል-አሕባሽ በዚህ መንፈስ እየሰራ ለአህል-ሱና ዋል-ጃማኣ በዓለም ሁሉ ውስጥ ድልድይና ሙጫ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ነው፡፡ የማህበሩ አንድ ድረገፅ ስለ ስራው ስነዘዴና እስላማዊ አንድነትን ለማምጣት እንዴት መሰራት እንዳለበት ለተጠየቀው ጥያቄ ሲመልስ የተናገረው፣ “በለስላሳ ቃላት፤ በመካከል መንገድ ጥበብ፤ በጨዋነት ሰበካ ነው በማለት ነበር፡፡ እንዲህ ነው ጉዞአችን የጀመረው በመተባበርና በግልፅነት፣ እንደዚህ ነው ዓለም አቀፍ ማህበር ለመሆን የበቃበነውና በዓለም ሁሉ ዙሪያ ያሉትን ሙስሊሞች ለመወከል የቻልነው፣ እቅዳቸውም ሙስሊሞች ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ ለእነርሱ ይህንን ትምህርትን በመስጠት ነው፡፡” 

የኢትዮጰያኖቹ መልእክቶች በሁለት አቅጣጫ ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ይህም አንደኛ፡ ለሙስሊሞች እንዲሁም ሁለተኛ፡ ሙስሊም ላልሆኑት ነው በማለት ፕሮፌሰሮቹ አስቀምጠዋል፡፡ በመጀመሪያ ለሙስሊሞቹ ያለው መልእክት በማያስገርም ሆኔታ ከበድ ያለ ነው፡፡ ከመጠነኛነት ባሻገር ከተቃዋሚው ክንፍ በተለይም ከዋሃቢያ ጋር ትንቅንቅ ያለበት ነው፡፡ ትንቅንቁም በትክክል በለስላሳ ቃል አልተላለፈም፡፡ የአል-አሕበሽ ሰዎች ተቃዋሚ ባላንጣዎቻቸው የሆኑትን እስላሞች በአብዛኛው የሚተረጉሟቸው እንደ ከሃዲዎች አድርገው ነው፣ እንዲሁም ከእስላም ማህበረሰ ሰብ ውስጥ ያገልሏቸዋል፡፡ እነርሱም በቃላት ጦርነቶቻቸው ውስጥ የሚቃወሙት ፓለቲካዊ እስላማዊነትን ጭምር እንደሆነ ጆርናሉ ያስረዳል፡፡ ስለዚህም ከፖለቲካዊ እስላማዊነት ጋር በተግባር የተያያዙትን የሳውዲ አረቢያውን፣ ሱዳንን እና ኢራንን አካሄድ ይነቅፋሉ፡፡

በሌላ ጎኑ ደግሞ መልእክቱ የተነጣጠረው ሙስሊምም ላልሆኑት ነው፣ መልእክታቸውም የዓለም አቀፍ ሰብዓዊነትነት ሃሳብ በማስተላለፍ ሁልጊዜ በመመጣጠን (በመቻቻል) መንፈስ ነው፡፡ በዚህ በኩል የማህበሩ ግብ የሰውን ልጆች ሁሉ ማገልገል እንደሆነና በእነርሱም አጠራር አል-ባሻሪያ ጃማኣ ወይንም ጃሚ አል-ናስ እንደሚባል ጆርናሉ አስቀምጧል፡፡ ሙስሊም ያልሆኑት ጥቂቶች በእስልምና ማህበረ ሰብ ውስጥ በመመጣጠን በሚያምኑት ሙስሊሞች ዘንድ ሙሉ የሆነ የመከበር መብት አላቸው ወይንም ከበሬታ አላቸው፣ ይሉና ቀጥሎም “ይህ ነው ለሁሉም የሚመች እስልምና” ይላሉ፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ የመንግስት እውቅናና አረባዊነት (ሁለቱም) እንደ የጋራ መብት ሆነው ሊካሄዱ ይችላሉ የሚልም እምነት አላቸው፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካን በተመለከተ አል-አሕህሾች የሚመለከቱት ሃይማኖትንና ፖለቲካን ተነጣጥለው መሄድ እንዳለባቸው  እንደሆነ ስለዚህም የእነርሱን እንቅስቃሴ ከማይቃወም ጋር ምንም ግጭት እንደሌላቸው የምርምሩ ጽሑፍ ያስረዳል፡፡ እነርሱም ከሶሻሊስቶችም ሆነ ከዓለማውያንን ጋር አብሮ ለመስራት ችግር የለባቸውም እንዲሁም የእስላም አክራሪነትን ለመቃወም የሚቆመውን ሁሉ እንደሚደግፉ ያስረዳሉ፡፡ አል-አሕበሾች ያሳወቁትና የገለፁት ሕጋዊ የሆነውን የተመሰረተ መንግስት እንደማይቃወሙ ነው፤ በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባት የእነርሱ ስራ አይደለም፤ በእርግጥም መሪዎችን በመግድል ለመለወጥ መነሳሳት የእነርሱ ጉዳይ አይደለም በማለት እነፕሮፌሰር ኤሊሪች አስረድተዋል፡፡

ለማስታወስም ያህል በክርስትያን-እስላም ሊባኖስ ውስጥ ኢትዮጵያውያኖቹ ብዙውን ሐሳባቸውን ስራ ላይ አውለውታል፡፡ እነርሱ በፖለቲካ ውስጥ ይሳተፋሉ በወረዳም እና በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም ይህንን የሚያደርጉት የመንግስትን ስርዓት በመደገፍ ብቻ ነው፡፡ በቤይሩት ብዙ ክርስትያን በሚኖርበት አካባቢ ቅርንጫፍ ቢሮ ማህበሩ ለምን እንደከፈቱ ሲጠየቁ አድናን አል-ታራቡልሲ የመለሰው እንደሚከተለው፡- “ሁሉንም ሕዝብ ለማገልገል እና የእስላም-ክርስትያን መልካም አብሮ መኖርን ለማስፋፋት ነው” በማለት ነበር፡፡ የአል-አሕበሽ ድርጊቶችና አመለካከቶች ብዙውን ጊዜ በክርስትያን መሪዎች ተመስግኗል፡፡ ከብዙ በጣም ጠቃሚ ምሳሌዎች ውስጥ፣ የታሪክ ተመራማሪዎቹ የጠቀሱት የፓርላማው ምክትል ሊቀመንበር የኤሊ ፋራዝሊን ቃላት ነው፡ “የእስላማዊ መረዳዳት ማህበር ፕሮጀክቶች በተባረከው እንቅስቃሴዎቹ ስሙን አስከብሯል፡፡ በእነርሱና በመሪዎቻቸው መካከል የመልካም ወዳጅነት ትስስር አለ እኛም ማህበሩን የምንመለከተው በሊባኖስ ውስጥ እንደ ተረጋጋ የአገር አቀፍ ድርጅት ምልክትና ምሰሶ አድርገን ነው ብሏል”፡፡ ኢትዮጵያኖቹ በእነርሱ በኩል ሊባኖስ ሙሉ እና ህጋዊ በእርግጥም ምሳሌ የምትሆን የራሷ ክልል ያላት የሕዝብ አገር ናት በማለት ይናገራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የሊባኖስን አገር ወዳድነት ማለትም “ዋራኒያ ሉብናኒያ”፣ እንደ ማህበረ ሰብ መሰረት አድርገው  ያመሰግናሉ፡፡ በፖለቲካል ድርጅትነት ደግሞ እንደ ባዝ ዓይነት (ሴኩላር) ዓለማዊ አረባዊነትን ያበረታታሉ፡፡ እነርሱም ድብልቁን “የጋራ መስመር” (አል-ማሳር አል-ሙሽራክን) እንዲሁም እንደ “እውነተኛ የራዕይ ስልት” ብለው እንደሚጠሩት ጆርናሉ አስቀምጧል፡፡

እነ ፕሮፌሰር ኤርሊች ያቀረቡት ታሪካዊ እውነታ እንደሚያስረዳው የማህበሩ ወርሃዊ ማናር አል-ሁዳ በሊባኖስ ውስጥ የበዓላትን ጊዜዎችን እና የሁሉም አረብ በዓላትን እና ዓመታዊ በዓላትን እንደሚመራ ነው፡፡ የማህበሩ ትምህርት ቤቶች የሶርያውን የሐፊዝ አል-አሳድን በጥቅምት 1970 ወደ ስልጣን መምጣትን እንደ ዓመታዊ በዓል አድርጎ ማክበርን ልማዱ አድርጎታል እንዲሁም የባዝ አረብ የፓን አረብን መፈክር “የተባበሩት አረብ መንግስታትን ሐሳብ” እንደሚያሳይበት አስቀምጠዋል፡፡

አል-አሕባሽ ለምዕራባዊው ማህበረሰቦች ያለው መልእክት ደግሞ በተለይም እስላማዊ ማህበረሰቦችን ለያዙት የመተባበርና አብሮ የመኖር ጥሪ እንደሆነ ሊቃውንቱ ሲያቀርቡ፤ ድርጅቱ የእስልምናን ምስል እንደ የሞራል ምሰሶ ለማሳየት እንዳቀደና አክራሪነት ያንን እንደማያሳይ እንደሚያምኑ አስቀምጠዋል፡፡ ስለዚህም አል-አሕበሾች አክራሪነትን አይቀበሉም፡፡ ኢትዮጵያኖቹ በአሜሪካና በዮሮፕ ውስጥ ስላላቸው ዕቅድ ተጠይቀው የመለሱትን መልስ ፕሮፌሰሮቹ ከድረገፃቸው ላይ በመጥቀስ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፡ “በሌላው የዓለም ክፍል ውስጥ እንደምናደርገው የሃይማኖት ድንቁርና በሚሰቃዩት መካከል የሃይማኖትን እውቀት ማሰራጨት ነው እንዲሁም እነዚያን አክራሪዎችን እስልምናን በአሉታዊ መንገድ ለመወከል የሚፈልጉትን ለማስጠንቀቅ ነው” እንደሆነ አሳይተዋል፡፡ የአሜሪካ ዬሮፕና አውስትራሊያ መንግስታትም ኢትዮጵያውኖቹን በአገራቸው ሙስሊም ሕዝቦች መካከል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በደስታ እንደተቀበሉት ሊቃውንቱ ሲዘግቡ በአል-አሕበሽ ዓይን ውስጥ እነዚህ አገሮች ሻሃባዎችን ተቀብሎ እስልምና እንዲገነባ እንደረዳው ልክ እንደፃድቁ ኢትዮጵያዊ ንጉስ “ነጃሺ” ናቸው እንደሚሉም የታሪክ ሊቃውንቱ አስቀምጠዋል፡፡

ከዋሃቢያ ጋር ጠላትነት         

የአል-አሕበሽ መሰረታዊ እምነቶች ከዋሃቢያ በጣም ይለያሉ፣ እንዲሁም የእስልምናን ፖለቲካዊ የበላይነት ለማስፈን ከሚፈልጉት ከሌሎቹ ሁሉ በጣም ይለያሉ፡፡ የዋሃቢያ መስራቾች በጽሑፎቻቸው ነገር ግን እዚህ ቦታ ላይ ልናብራራው አሁን በማንችለው በአብዛኛው የሚዘጉትና (ለማንሳት የማይፈልጉት) የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ቅን ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ አል-አሕበሽ በሊባኖስና በዓለም አቀፍ መድረክ ብዙ ታዋቂነትን ባገኘ ቁጥር በተለይም ከ1990ዎቹ ጀምሮ ከዋሃቢያ ጋር ያላቸው የቃላት ጦርነት በጣም እየተባባሰ መጣ፡፡ የግል መሰረታዊ አመጣጡ በ1940ዎቹ ውስጥ ከኢትዮጵያ እንደነበር በጣም ግልጥ ነው፤ ይሁን እንጂ ሼክ ዩሱፍ አንድ ጊዜ በ1976 ከሐረር ወደ መዲና እንደገና ከሄደ በኋላ ይህን ዋና ጠላቱን ሼክ አብደላን ለማጥቃት ከአስጠጉት አጋሮቹ (ከነሳውዲ አረቢያ) እገዛ በማግኘት ጠላቱን የሚቃወምበትን ዕድሎችን ሁሉ ጊዜ ሳያጠፋ ተጠቅሞባቸዋል፡፡ የሳውዲ የሃይማኖት መሪዎችን ያሳመነው ሐረር ከኢትዮጵያ ቀንበር ውስጥ ነፃ ወጥታ የእስላም ማዕከል እንድትሆን የነበረውን እንቅስቃሴ ለማቆም ከበስተጀርባው ሆኖ ከኃይለስላሴ  መንግስት ጋር ይሰራ የነበረው ሼክ አብደላ ነው በማለት ነበር፡፡ ይህ የሐረር ፖለቲካዊ እስላማዊ እንቅስቃሴ መክሸፍ ውንጀላ በሼክ አብደላ እና በተባባሪዎቹ ላይ “ፊትናት ኩሉብ” በመባል ይታወቃል፡፡ ማለትም “የክለቡ ወንድማማቺያዊ ግጭት”፡፡ ዋሃቢስቶች እና ደጋፊዎቻቸው ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ይህንን የሐረርን እስላማዊ ግዛት እንቅስቃሴ መክሸፍን እንደ መሰረታዊ ኃጢአት አድርገው ደጋግመው ያነሱታል፡፡ አል-አሕበሾች በበኩላቸው ይህንን የ“ፊትናት ኩሉብ”ን ታሪክ አይቀበሉትም፣ ይህንንም የሚያደርጉት ያለምንም ችግር ለዝርዝሮች ሳይጨነቁ ነው፡፡ እነ ሼክ አብደላ የሼክ ዩሱፍን እራሱንና የዋሃቢዝምን ተፅዕኖ  የሚከሱበት አንድ ነገርም ቢኖር በኢትዮጵያና በሐረር ውስጥ ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ (1936-1941) ያደረጉት ተፅዕኖ (ከሙሶሎኒ ጋር በመስማማት) እስልምና በሐረርና በኢትዮጵያ ላይ ይኖር የነበረውን ጥሩ ነገር አክሽፈዋል በማለት ነው፡፡ (ይህንን በተመለከተ “ግመል ለሙሶሊኒ” በሚል ርዕስ ፕሮፌሰር ኤርሊች ከጻፉት ላይ ያቀናበርነውን አስገራሚ እውነተኛ ታሪክ ከክፍል ሦስት ቀጥሎ ለአንባቢዎች እናቀርበዋለን)፡፡

በ1980ዎች  መካከል ላይ አህበሾች ከእስላማዊ ጠላቶቻቸው ከዋሃቢዎችና እንዲሁም  በሊባኖስ ካሉ ከሌሎች ቡድኖች ጭምር ጋር መጋጨት ጀመሩ፡፡ ምንም እንኳን የአንድ ጎን እንቅስቃሴ ቢሆንም በሳውዲ አረቢያ ባለው የዋሃቢዝም ድርጅት ዘንድ ትኩረትን ስቦ ነበር፡፡ ሼክ ዩሱፍ በመዲና እያለ በሚኖርበት በሳውዲ ውስጥ የሚችለውን አድርጎ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በሐምሌ 1986 ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ዋና የእስላም ዳኛ ሼክ አብ አል-አዚዝ ቢን አብደላ ቢን ባዝ (1999) በአል-አሕባሽ ላይ ፋትዋን አዘዘ የሚለውም እንደሚከተለው እንደነበር የታሪክ ሊቃውንቱ አቅርበዋል፡-

‘የአል-አሕበሽ ድርጅት የተሳሳተ ቡድን ነው እርሱም ከአህል አል-ሱና ዋን-ጃማአ ውጭ ነው፡፡ በእነርሱ ፋትዋ ላይ ማንም መተማመን የለበትም ምክንያቱም እነርሱ አፈንጋጮች ናቸው የእነርሱም ቃላት ቁርአንንና ሱናን ይቃረናሉ፡፡ ማንም እነርሱን ማመን የለበትም ሁሉም ስለ እነርሱ ማወቅ አለበት እንዲሁም ማንም ቡድን ከእነርሱ ጋር መገኘት የለበትም”

ይደረግ የነበረው የቃላት መወራወር በስርዓት ለመግለጥ የማይቻልና በጣም ብዙ ነበር፡፡ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የቃላት ውርውሩ ገና ዓመፅ  እንዳልነበረበት ተገልጧል፡፡ በሕዳር 1992 ለምሳሌም የሳውዲው ጆርናል አል-ሙስሊሙን (ከአብደል አዚዝ ቢን ባዝ የተያያዘው) የተከታታይ አንቀፆችን ያወጣ ነበር፡፡ ይህም ከሐረር ብቻቸውን መጥተው በሊባኖስ ውስጥ አዲስ የሆነ የሃይማኖት ማህበረሰብ መመስረት ስለቻሉት “በእንግዶቹ ኢትዮጵያውያን ላይ” እንደነበር በጆርናላቸው ላይ ሰፍሯል፡፡ የአል-ሙስሊሙን ጋዜጠኛም አል-አሕበሾች የእስልምናን ልማዳዊ ልብስ (ቀሚስ) ያልለበሰችን ሴት ስለምን እንደሚቀበሉ ናዚር ሃላቢን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ችሎ እንደነበርና ያገኘውም መልስ፤ አል-አሕበሾች ሴቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን እንደሚመርጡና ሴቶች ጂንስ መልበስ ይችላሉ (“ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለው”) የሚል ነበር፡፡ ቀጥሎም ማህበሩ በፆታዎች መካከል ነፃ የሆነ ንግግርን በማደፋፈራቸው (በማበረታታቸው) ክብር እንደሚሰማው የሰጠውንም መልስ ምሁራኖቹ አሳይተዋል፡፡

በ1994 የአል-አሕበሽ - ዋሃቢ የቃላት ልውውጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ይህም ሼክ አብደላ መጽሐፉን በቤይሩት ውስጥ ባወጣበት ጊዜ ነበር፡፡ የመጽሐፉም ስም “The Sublime Sayings in Exposing the Wrongs of Ibn Taymiyya”. ይህ በዋሃቢዝም መንፈሳዊ አባት ላይ በጣም ከባድና ከፍተኛ ጥቃት ነበር በዚህም ውስጥ የአል-አሕበሽ መሪ የገለጠው “የኢብን ታይሚያ” እውቀት ከአዕምሮው በላይ እንደሆነ ነበር፡፡ እርሱም ከእስልምና አጠቃላይ ስምምነት ላይ በስልሳ ነጥቦች (ወይንም ጉዳዮች) እንዳፈነገጠ ገልጧል፡፡ የሼክ አብደላ መጽሐፍ እንደገለጠውም ኢብን ታይሚያ ብዙ ሰዎችን እንዳሳሳተ ይህም ስህተት በብዙ ሊቆች ዘንድ የኑፋቄ አዳዲስ ነገሮችን ማስፋፋቱ እንደተጋለጠ መጽሐፉ ማስቀመጡን ጆርናሉ ያስረዳል፡፡ በዚያው መጽሐፍ ላይ ሼክ አብደላ ያጠቃው አብደ አል-ዋሃቢንም ጭምር እንደሆነ ይህንንም ሲያደርግ የዋሃቢያን መስራች የከሰሰው ከቁርአን ወይንም ከሱና መጡ ያላቸውን አባባሎችን እራሱ በመፍጠሩ ነበር፣ ከዚህም  ባሻገር አል-ዋሃቢ የሱፊ እስላም ምሰሶ የሆኑትን ጉዳዮች ማለትም የመቃብር ቦታዎችንና የቅዱሳንን የመታሰቢያ ቦታዎችን መጎብኘትን መከልከሉንም በተመለከተ እንደሆነ ሊቃውንቱ ገልጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኢብን ታይሚያና የአብደል-ዋሃብ ተከታዮች መከራከሪያ የሚለው የእነርሱ ትምህርት የሳላፊዎች ትምህርትና እራሳቸው ሳላፊዎች ናቸው የሚል ነበር ማለትም እነርሱ እስልምናን በመሰረቱት መስራቾቹ መንገድ የሚሄዱ ናቸው የሚል ነበር፡፡ ይህንን አባባላቸውን አንስቶ ሼክ አብደላ የጸፈው የማይረባ አባባል ነው በማለት  እንደሆነ ጆርናሉ ያሳያል፡፡ የእነርሱ ማለትም የዋሃቢያ አራማጆች እንቅስቃሴ ሰላፊያ አይደለም፡፡ ነገር ግን አማኞችን ወደ ውሸት ፈጠራዎች ይመራቸዋል እንዲሁም ከመስራቾቹ ትውልዶች እጅግ በጣም አርቆ ይወስዳቸዋል በማለት ሼክ አብደላ ይከራከራል፡፡

ለሼክ አብደላ መጽሐፍ መልስ የተሰጠው መጽሐፉ ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ በ1995 እንደነበር እነ ፕሮፌሰር ኤርሊች ጠቅሰው ይህም በሲድኒ አውስትራሊያ የዋሃቢ መሪ በሆነው በአቡ ሱጋይብ አብድ አል-አዚዝ አል-ማላኪ “The Sublime Sayings in Exposing the Wrongs of the Ahbash Group”.  የሚለውን መጽሐፍ አሳትሞ እንደሆነ አሳይተዋል፡፡ የመጽሐፉም አንዱ ዋና ዓላማ የአል-አሕበሽ ድርጅት ሙስሊም ካልሆኑት ጋር ስላለው ትብብር ለማጋለጥ ነበር፡፡ ይህንን መጻፉ አያስደንቅም ነበር ምክንያቱም እነርሱ በሊባኖስ እና በክርስትያኖች ሁሉ ብዙ ምስጋናን አግኝተው ነበርና ነው፡፡ እነርሱም ልክ አንድ መንግስት እንደሆኑ አድርገው በመቁጠር ከክርስትያኖች ጋር አብረው በዓላትን ያከብሩና ባህላቸውንም ይጋሩ እንደነበር፡፡ ከ”ሊባኖስ ክርስትያን ወጣቶች” እንቅስቃሴ ጋር የ”ደስታና የፈገግታ” ክብረ በዓላትን በማዘጋጀት ይተባበሩ እንደነበር፡፡ አቡ ሲጋይብ ይህንን ሁሉ ግምት ውስጥ አስገብቶ የጻፈው “ከአል-አሕበሽ” የሙዚቃ ቡድን ጋር በአህል አል-ሱና ዋለ-ጃማኣ ማስተር ስር የእስላማዊ ሙዚቃዎችን በኤሌክትሪክ ከበሮ በመጫወት ምዕራባዊ ድምፅ እንዲኖረው ያደርጋሉ በሚል የትችት ቃል ነበር፡፡ መጽሐፉም ስለ አል-አሕበሽ በሌሎች የዋሃቢ መሪዎችና የሙስሊም ወንድማማች ቡድን መሪዎች በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ የተጻፉ ጥቅሶችን ያካተተ ነው፡፡ ሼክ ሰይድ ሻባን ለምሳሌም ያህል የአል ታውሂድ አል-ኢስላሚ በሊባኖስ ውስጥ አል-አሕባሽን የጠራው “የእስልምናን መንፈስ የለበሰ ቡድን” በማለት ሲሆን በግብፅ ሚኒስትሪ ውስጥ የአውካፍ ባለስልጣን የሆነው ፊኪሪ ኢስማኤል በሃዘን የተናገረው በአህል አል-ሱና ዋል-ጃማኣ ውስጥ ክፍፍል በማለትና ውንጀላውን በሙሉ በአል-አሕባሽ ላይ በማድረግ ነው፡፡ እርሱም የጻፈው እንደዚህ ዓይነት መሪ ሊቆችን እንደ ሐሰት አስተማሪዎች ለመክሰስ ለሙስሊሞች ምንም ምክንያት የላቸውም ካለ በኋላ የሚከተለውንም ጨመረ፡-

“እንግዳ የሆነ ሰው ከኢትዮጵያ ምድር ሲመጣ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ ነው፤ በባህርዩ እና በሐሳቡ የተለየ ሰው ነው፣ እንዲሁም በሚሰራበት በስነ ዘዴው አህል አል-ሱናን ከፋፍሎ ለመቁረጥ .... እርሱ የሹውባይ አክራሪ እና በአንድ በኩል አረብን የሚጠላ ሲሆን በሌላ ጎኑ ደግሞ ሺያ ነው፣ በመሆኑም በሌሎች ላይና በሱና ላይ ቂም በቀልን የያዘ ነው”

የዋሃቢው መልሶ ጥቃት ሦስት አቅጣጫ ያለው እንደነበር፡፡ አል-አሕበሽን የሚወነጅሉት እነርሱ የሱፊ ብዙ አማልክት እምነት ጋር የተደባለቀ በማለት ነው፣ ሺርክ፣ ከሺያ ድብቅ የፀረ ሱና ስነ ዘዴ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ዋሃቢዎች አል-አሕበሾችን የሚከሱት የሺያይቶችን ታሪካዊ ጠላትነት እያራመዱ ነው በማለትም ጭምር ነው ይህም ከዑማያዶች ጋር ሲሆን ያንንም የሚያደርጉት ሱናን ለመዋጋት ከሺያይቶች ጋር ለመተባበር ብለው እንደሚሉ ሊቃውንቱ ታሪክን ፈልፍለው አስቀምጠዋል፡፡ የአል-አሕበሽ ክርክር ዋሃቢዎች እንደሚሉት ከሆነ እነርሱ አሻሪዎች ስለሆኑ ነው ስለዚህም እነርሱ የሚወክሉት የሱኒን ስምምነት መሆኑን እና ይህም ለተሳሳተ እስልምና መሸፈኛ ብቻ ነው፡፡ እነርሱም ልክ እንደ ቀድሞዎቹ ሹቢያዎች እንቅስቃሴ የአረቦች ጠላቶች ናቸው ማለትም ለአረቦች ምንም ዓይነት የተለየ ዕድል ሊኖራቸው አይችልም በማለት ለሚክደው እንቅስቃሴ፡፡ ከዚህም በላይ አል-አሕበሾች ሼክ አብደላ የቋራይሽ ዝርያ አለው የሚሉትም ስህተት ነው ይሉና፣ እርሱ ኢትዮጵያዊና የውጭ አገር ሰው ነው (ጠጉረ ልውጥ ነው) በማለት እንደሚናገሩም አስፍረዋል፡፡

የዋሃቢ ፀረ-አል-አሕበሽ ወቅታዊ ጽሑፎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል በማለት እነ ፕሮፌሰር ኤርሊች ያሳስባሉ፡፡ የዋሃቢዎች ጽሑፎች ወደ እንደዚህ ዓይነት የዘርና የጎሳ ልዩነቶች ላይ የሚመጡት በጣም ጥቂት ጊዜዎች ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያውያኖቹ ደጋፊዎች በዓለም ዙሪያ ያሉት ከዘር ያለፈ ዓለም አቀፍ እስልምና ለመወከል ስለሚፈልጉ ተቃዋሚዎቻቸው በዘር ልዩነት ወጥመድ ውስጥ በግልጥ እንዳይወድቁ ይጠነቀቃሉ፡፡ ስለዚህም የሼክ አብደላ አመጣጥ በእርሱ ላይ እንደተቃውሞ የሚነሳው በጣም በጥቂት ጊዜያት እንደሆነና ይህም በተዘዋዋሪና በጣም በረቀቀ መንገድ እንደሚደረግ የታሪክ ሊቃውንቱ ጥናት ይጠቁማል፡፡  ከእንደዚህ ዓይነቱ አሳሳቢ ነገር ውጭ የሆነው ፊኪሪ ኢስማይ ነው፣ እርሱም በጣም የታወቀው የሰላፊ ሰባኪ የነበረውና ግብፃዊው አህመድ ሻላቢ አል-አሕበሾች ለምን በጣም ጠባቦች ሆኑ በማለት እንደሚከተለው አብራርቷል፡ “እነርሱ በእስላማዊ ሐሳቦች ላይ ሰፋ ያለ አመለካካት የላቸውም ምክንያቱም በመሪያቸው በአብደላ አል-ሐባሽ የተነሳ ነው፣ እርሱም የወጣው መሰረታዊ የሃይማኖት ትምህርት ከሌለበት ቦታ ከኢትዮጵያ ነው፣ ስለዚህም ነው የእርሱ ቡድን በአንደዚህ ዓይነት በጣም ጥንታዊ (ኋላ ቀር) ፅንሰ ሃሳብ ውስጥ ያሉት” በማለት እንደተናገረ ጆርናሉ ይገልጣል፡፡

የሳላፊ ዋና መሪ የሆነውና በዮርዳኖስ የዋሃቢ ነክ እንቅስቃሴ መሪ ሼክ አቡ ማሊክ (መሐመድ ሻክራ) በድረ ገፅ የቃለ መጠይቅ ላይ ሼክ አብደላን አጥቅቷል፣ እርሱም ሼክ አብደላን የገለጠው “የቆዳ ሕመም ያለበት እንግዳ ቁራ” በማለት ነው፡፡ በተጨማሪም የተናገረው ኢትዮጵያውያኖች ልክ እንደ አይሁዶችና ክርስትያኖች ከሃዲዎች (ኢንፊደልስ) ናቸው በማለት እንደነበረ ተጠቅሷል፡፡

ሼክ አብደላ ለእንደዚህ ዓይነት ንግግሮች መልስን የሰጠው እንዴት ነበር? ብለን ልናነሳ ለምንችለው ጥያቄ የታሪክ ተመራማሪዎቹ ያስቀመጡት ሃሳብ እርሱ የዘርን ጉዳይ ከማጉላት እራሱን ያገለለ መሆኑን ነው፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያዊነቱ ይኮራል ይሁን እንጂ እስልምና ስለ ቆዳ ቀለም ትኩረት አለመስጠቱን እንደተናገረ አስረድተዋል፡፡ በሼክ አብደላ ተከታታይ ትምህርት ውስጥ በማናር አልሁዳ ላይ በታተመው እርሱ የጻፈው፡

“ነቢዩ ስለዘር ጉዳይ ጠቃሚነት መመልከት ወይንም ማሰብን ምንም  አልተናገረበትም፡፡ ዑሳማ የዛይድ ልጅ ነበር እርሱም የሐሪታ የልጅ ልጅ ነበር (እርሱም ከየመን የነበረ ኢትዮጵያዊ ነበር)፡፡ ነቢዩ ዛይድን አሳዳጊው ከነበረችው ከኢትዮጵያዊቱ ከዑም አይማን ጋር አጋብቶት ነበር ዑሳማም ጥቁር ነበር፡፡ የነቢዩ የአጎት ልጅ አል ፋዲ ኢብን አል አባስ በጣም ቆንጆና ቀላ ያለ ቆዳ ነበረው፡፡ ነገር ግን ነቢዩ ከዚያ ጋር ምንም ጥቅምን አላያያዘበትም ነበር፡፡ እርሱም መንገዱን ወደ መካ ባደረገበት ጊዜ እርሱ ዑሳማን እንደ አብሮ ሂያጅ ይዞት ይሄድ ነበር ምክንያቱም ዑሳማ እስልምናን በቅድሚያ ተቀብሎ ነበርና፡፡ ያኔ ብቻ ነበር እርሱ አል-ፋዲን የወሰደው፡፡” የሚለውን ታሪክ ዘጋቢዎቹ አቅርበዋል፡፡

የአል-አህበሽ ጆርናል ማናር አል-ሁዳ የኢትዮጵያውያንን መልእክቶች በዋሃቢ ላይ የሚያስተላልፉትን ጥቃት ጨምሮ ለማስተላለፍ ሌላው አንድ መድረክ እንደነበረ የታሪክ ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡  እነዚህ ጥቃቶች በጣም ከባድ እየሆኑ የመጡት ከኒዛር አል-ሃላቢ ግድያ በኋላ ነበር፡፡ ዋሃቢዎች አሁን አክራሪዎችና አሸባሪዎች ተብለው መጠራት ጀመሩ “እስልምናን በሃሳባቸውና በድርጊታቸው እያጠፉ ላሉት እኛ እራሳችንን ለመስጠት አልተዘጋጀንም፡፡” እንዲሁም “የእነርሱን ጥቁር አክራሪነት ሐሳብ እንዲያስፋፉ አንፈቅድላቸውም” የሚሉ መግለጫዎችን ያወጣሉ በዚህም መሰረት ከዓለም ዙሪያ ያሉ አንባቢዎች ለእነዚህ ቃላቶች አብረዋቸው የሚቆሙ መሆናቸውን የሚገልፁ ደብዳቤዎችን ልከውላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ሙስሊሞች ዋሃቢን በግልጥ (በአደባባይ) የካዱ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ እንደካዱ ማስረጃ እንዳለ ጽፈዋል፡፡ ይህንንም በመቀጠል አንዳንዶች  “አማኞችን በነቢዩ ትክክለኛ መንገድ ለመምራት የእናንተ ጆርናል በጣም ጠቃሚ ነው” ቀጥሎም፣ “እንዲሁም የአፈንጋጮቹን የተሳሳተ ፈጠራዎችንና በእግዚአብሔር ስብዕና የሚያምኑትን ውሸቶቻቸውን ለመዋጋት” ይጠቅማል በማለት ከሕንድ አንድ አንባቢ እንደጻፈ ገልጠዋል፡፡

አል-አሕባሽ እንዲሁም መልእክቱ እስልምና ከሌላው ጋር መኖር የሚችል እምነት ነው የሚል ሆኖ እያለ በኢትዮጵያውን ሙስሊሞች ዘንድ ለምን ተቀባይነት አልነበረውም? የሚለው ጥያቄ የኢትዮጵያ ሕዝብን ሁሉ ሊያሳስብና ሊያነጋግር የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ ለዚህ ጥያቄ መልሱ ከዚህ በላይ ካስቀመጥኳቸው የይሆናሉ መልሶች ወደ ሁለተኛው የሚያዘነብል መሆኑ ምንም ጥርጥር የሌለው ነው፡፡ ይህንንም በጊዜው እንመለከተዋለን፡፡

እነ ፕሮፌሰር ኤርሊች እንደሚሉት የኢንተርኔት መምጣት ለዚህ የውስጥ እስላማዊ ትግል (ጦርነት) በጣም ጠቃሚ የሆነ መድረክን እንደፈጠረለትም ነው፡፡ የዋሃቢ-አሕበሽ ክርክር በእስላማዊ ድረገፆች የክርክር ዋና ርዕሰ ጉዳይ ከሆኑት መካከል አንዱና በጣም የተጋጋለው እንደሆነ ጆርናሉ አስቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያውያኖቹ የራሳቸውን ድገ ገፅ (ዌብሳይት ከፍተዋል) “የደህንነት ጀልባ ኦርግ” የሚባለውን (www.safeena.org), ምናልባትም የመጀመሪያዎቹን ሙስሊሞች ወደ ደህንነታቸው ቦታ ኢትዮጵያ የወሰዳቸውን ጀልባ ለመጥቀስ ይሆናል፡፡ ጠላቶቻቸውም የእነርሱን የሚቃወም “ፀረ ሀበሺ ኮም” www.antihabashis.com የሚለውን ዌብሳይት ከፍተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማለቂያ የሌላቸው ክሶችን ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በተለያየ መልኩ እየተጨማመሩ ድረ-ገፆቹ እየሰፉ እንደሄዱ ነው፡፡

የኢንተርኔት ጦርነቱ በተለያየ አቅጣጫ ቀጥሏል ዋሃቢዎች ኢትዮጵያውያኖቹን ከአሜሪካ ጋር እስልምናን ለመዋጋት የቆሙ ናቸው በማለት አሁንም እንደሚከሷቸው የታሪክ ሊቃውንቱ ገልጠዋል፡፡

የአል-አሕበሾችን ስህተት በማጋለጥ አቡ ሱሃይብ አል-ማሊኪ ከቤይሩት የሆኑ ምሁራንን ለምስክርነት ጠቅሷል ሼክ አብደላ እስራኤል በ1982 ሊባኖስን ስትወር ፋትዋ እንዳወጣና ሕዝቡ እነርሱን እንዳይቃወም የከለከለ መሆኑን፡፡ ይህንን ፋትዋ በማውጣት “ሼክ አብደላ በክርስትያኖች ቁጥጥር ስር ወደሆነው ወደ ምስራቅ ቤይሩት ኮበለለ” የሚባል ወሬዎችን ሁሉ እንዳስወሩበት እነዚህ ምሁራን ይጠቅሳሉ፡፡

ከዋሃቢያ ጋር አንድ የሆነው ሌላው ዌብ ሳይት ኢትዮጵያውያኖቹ ማለትም አል-አሕበሾችን ከአሜሪካ ጋር እስልምናን ለመዋጋት የቆሙ ናቸው በማለት ከሷቸዋል፡፡ በአሜሪካ የምስጢር መዝገብ ውስጥ በዓረብ ዓለም ውስጥ ሁሉ ያሉትን የሙስሊም ወንድማማችነት እንዲያጠፉ የደገፉ መሆናቸውን ፣ እንዲሁም በእስራኤል ላይ ቅዱስ ጦርነትን የጠሩትን ሁሉ ጨምሮ እንዲሁም እነርሱን በአል-አህበሽ እንዲተኩ ጭምር ዘግቧል፡፡

ይህ ክፍል ሁለት በአጠቃላይ የሚያሳየው እስልምና ውስጥ ከአገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ የገነኑ ሁለት ርዕዮተ ዓለሞች መኖራቸውን፣ ሁለቱም መራራ ትግል እያካሄዱ እንደሆነ ነው፡፡ ከጽሑፎቹ ግልፅ እንደሆነው፡

አንደኛው፡ እስልምና ፖለቲካዊ መሆን አለበት፣ እስልምና ከሌሎች ጋር አንድ ላይ መኖር የለበትም፣ እስልምናን ያልተከተለ በእስላም አገር መኖር የለበትም፣ ይህንን ለማስፈን አክራሪነት እና ኃይልን መጠቀም ያስፈልጋል፣ ክርስትያኖችና አይሁዶች የእስልምና ጠላቶች ናቸው የተጠሉ ናቸው፣ ኢትዮጵያ የእስላም አገር መሆን አለባት የሚል ውስጣዊ እንቅስቃሴን የሚመራ በዓላማ የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ቡድን ሲሆን፤ ይህ የዋሃቢያው ክንፍ ነው፡፡

ሁለተኛው፡ የመጀመሪያውን የሚነቅፍና እስልምና ከሌሎች ጋር መኖር ይችላል፤ እስልምና ፖለቲካዊ መሆን የለበትም፣ እስልምናን ያልተከተለ ተከብሮ መኖር አለበት፣ አክራሪነት የእስልምናን ስም ያስጠፋል ትክክልም አይደለም፣ ከክርስትያኖችና ከአይሁዶች ጋር በሰላም መኖር እንችላለን የሚል፣ ኢትዮጵያ የመቻቻል ምሳሌ ናት የሚለውና በኢትዮጵያውያኑ ሼክ አብደላ የሚመራው የአል-አሕበሽ ክንፍ ነው፡፡

ታዲያ በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ተከታይ ያለው የትኛው ቡድን ነው? በቅርቡ የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍስ የተመራው በየትኛው ርዕዮተ ዓለም ተከታዮች ነው? የሚሉት ጥያቄዎች እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊያስብባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ሲሆኑ ትክክለኛ መልስ ልንፈልግላቸው ይገባናል፡፡ ወደ ጥያቄዎቹ መደምደሚያ ለመቅረብና ታሪካዊ እውነታ ላይ ወደ ተመሰረተ መልስ ለመሄድ የነፕሮፌሰርን ጆርናል ቅንብር ክፍል ሦስት በሚቀጥለው ጊዜ ይዘን እንቀርባለን፡፡

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ