አጫጭር ዜናዎች
እስልምና በኢትዮጵያ ውስጥ ከየት ወዴት?
በ ዳንኤል
ሰሞኑን በሀገራችን ውስጥ ትልቅ ትኩሳት ሆኖ የሰነበተ አንድ ብሔራዊ ጉዳይ አለ:: ይኸውም በእስልምና ውስጥ የተፈጠረው ክፍፍል እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ "መንግስት በኃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል" በሚል ከሙስሊሞች ዘንድ የተሰማው ተቃውሞ ነው:: ይህ ጉዳይ ሚያዝያ 9 ቀን 2004 ዓ.ም. በነበረው የፓርላማ ውሎ ወቅት ትልቅ የመነጋገርያ አጀንዳ ሆኖ ቀርቦ እንደነበር ይታወሳል:: በዚሁ እለት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሰፋ ያለ ጊዜ በመውሰድ ማብራርያ ሰተዋል:: በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደተናገሩት፥ በሃገራችን ለረጅም ዘመናት የቆየው ነባሩ የእስልምና እምነት ሱፊ ሲሆን የኢትዮጵያ ሙስሊም ሙሉ በሙሉ ሱፊ ነበር:: ስርዓቶቹ የነበራቸው የአድሎ ፖሊሲ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለፉት ዘመናት በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል በየትኛውም ዓለም በየትኛውም ሃገር ካለው የተሻለ መቻቻልና አብሮ መኖር ታይቶበታል:: ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለው እንደተናገሩት ሰለፊ የተባለው የእስልምና እምነት ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን ብዙዎቹ የአልቃኢዳ አሸባሪዎች ከእምነት አኳያ የሰለፊ እምነት ተከታዮች ናችው:: በኢትዮጵያ ውስጥም ለመጀመሪያ ጊዜ በአብዛኛው በባሌ እና በአርሲ አካባቢ የአልቃኢዳ ህዋስ ተገኝቷል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየመን፥ ግብጽ፥ ሊቢያ፥ ሶርያ እና ቱኒዝያ እየሆነ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመጥቀስ ሰለፊዎች በሃገራችን ውስጥ የቆየውን መቻቻል በማውገዝ እና በማጥፋት ሊያስከትሉት ያለውን አደጋ ጠቁመዋል::
ሰለፊ ወይም ብዙዎች እንደሚጠሩት ዋህቢያ በመባል የሚታወቀው የእስልምና ቡድን መሐመድ ኢብን አብዱል ወሃብ በተባለ ከ 1703 እስከ 1791 ዓ.ም. በኖረ የሳዑዲ ዓረቢያ ተወላጅ የተጀመረ ነው:: መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የሰለፊ እምነት ተከታዮች ግባቸው እስላማዊ የሆነ መንግስት መመስረት ሲሆን እስላማዊ ላልሆነ መንግስት አንገዛም የሚል አቋም አላቸው:: ይህንንም ዓላማቸውን ለማሳካት አመፅ ያነሳሳሉ፥ ሽብርና ብጥብጥ ይፈጥራሉ:: ሰለፊ (ወህብያ) የእምነት ነጻነት የሚባል ነገር አያስተናግድም:: በራሱ በእስልምና ውስጥም ቢሆን ሌሎች የእስልምና ቡድኖች መኖራቸውን አጥብቆ ይቃወማል፥ ከእርሱ ውጪ ያሉትንም ቡድኖች በከሃዲነት ይፈርጃል፥ ያስፈራራል፥ በአሳቃቂ ሁኔታም ይገድላል::
ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የኢትዮጵያ የፈደራል ጉዳዮች ሚንስትር ሚያዝያ 8 ቀን 2004 ዓ.ም. ሪፖርተር ከተባለ የግል ጋዜጣ ጋር ቃለምልልስ ባደረጉበት ወቅት እንደ ገለጹት ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰለፊዎች ዋና መፈልፈያ አወልያ በመባል የሚታወቀው የትምህርት ተቋም ነው::
"አወልያ ስራውን ሲጀምር ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለልጆቻችን ይጠቅማል በማለት ያደራጁት ተቋም ነው:: ይህ ተቋም እየሰፋ ሲሄድ በተለይም አንዳንድ የውጪ አገር መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በእገዛ እና በድጋፍ ስም ተቋሙን እየተቆጣጠሩት ሄደዋል:: በተለይም አረብኛ እናስተምራለን በሚለው የትምህርት ክፍል ከተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች አባት እና እናት የሌላቸውን ወጣቶች በማሰባሰብ እና በመመልመል የዋህብያን ትምህርት በቀጥታ ከመሐመድ ኢብን አብዱል ወሃብ የተጻፉትን መጽሐፍት በመጠቀም፥ ዝግ በሆነ ሁኔታ በምንም ዓይነት መንገድ ከውጪ እንዳይገናኙ ከውስጥ ብቻ ቆልፈው ወደ ውጪ በሚወጡበት ጊዜ ተናዳፊ እንዲሆኑ አሰልጥነዋል:: እስከዛሬ ከ 200 እስከ 300 የሚሆኑ ተማሪዎችን በዚህ ዓይነት መንገድ እስከ አራት ዓመት ድረስ አስተምረው እየተመረቁ እንዲሰማሩ አደርገዋቸዋል::" ይላሉ የፌደራል ጉዳዮች ሚንስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም::
ክቡር ሚንስትሩ አክለው እንደገለጹት በሃገራችን ውስጥ የእምነት ነጻነትን የሚቃወመው የዋህቢያ አመለካከት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴውም አለ:: እነዚህ ሰዎች ከራሳቸው አመለካከት በመነሳት እነርሱን የማይከተለውን በአደባባይ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳርጉ፥ የመቃብር ቦታዎችን፥ ቤተክርስቲያናትን እና መስጊዶችን በስፋት የማቃጠል ተግባር እየፈጸሙ እንዳሉ፥ እንዲሁም መንግስትም ጭምር እስላማዊ አይደለም በሚል ፀረ-ልማት እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉበት ሁኔታ እንደሚታይ ያስረዳሉ::
በሚያዝያ ዘጠኙ የፓርላማ ውሎ ወቅት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ "አሕበሽ" ስለተባለው የእስልምና ትምህርት ማንሳታቸው ይታወሳል:: እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ መንግስት አሕበሽ የሚባል ነገር አመጣብን የሚል ተቃውሞ ከሰለፊዎች ዘንድ መነሳቱ ተገቢ አይደለም:: ምክንያቱን ደግሞ ሲያስረዱ ነባሩ የእስልምና ተከታዮች (ሱፊዎች) እንደሚገልጹት አሕበሽ የሚባለው ከውጪ የመጣ ኃይማኖት አይደለም:: ኢትዮጵያዊው የሐረር የእስልምና አዋቂ ሼኽ አብዱላሂ በሃገራቸው መኖር ስላልቻሉ ወደሊባኖስ ሄደው የሱፊ እምነት አስተምህሮ ያራመዱበት እንደሆነ ከነባሩ የእስልምና ሊቆች እንደሚነገር አመልክተዋል:: የፌደራል ጉዳዮች ሚንስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደገለጹት ሼኽ አብዱላሂ ኢትዮጵያዊ እንደመሆናቸው መጠን (አረቦቹ ከኢትዮጵያ የሄደውን ሰው በሙሉ አሕበሽ ነው የሚሉት) ከእሳቸው ጋር በተያያዘ የሚሰጡት ትምህርት የአክራሪነትን አስተሳሰብ የማይከተል በመሆኑ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተው በዓለም ደረጃ ወደ 54 ሃገሮች አካባቢ ጭምር የሚያስተምሩት ነው:: ትምህርቱ ነባር የእስልምና አስተምህሮዎችን ይከተላል:: ተለየ ተብሎ የሚጠቀሰው አሕበሽ የሚለው አገላለጽ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ነው:: ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ከሆነ ምሁር ከወሰዱት በኋላ ሙስሊም ሊቃውንት መልሰው አምጥተው ያስተማሩት ነው እንጂ ከእምነቱ የወጣ አይደለም ይላሉ ክቡር ሚንስትሩ::
እንግዲህ አንባቢ ሁሉ ሊገነዘብ እንደሚችለው የሰለፊዎች ዋና ትግል በአንፃራዊ ሁኔታ "ሰላማዊ" ተብሎ ሊገለፅ የሚችለውን ነባሩን የሱፊ እስልምና አክራሪ በሆነው እና ለሌሎች ነጻነት ፈፅሞ እድል በማይሰጠው በዋህቢያ ትምህርት መተካት ነው:: እየታዩ ያሉ ሁኔታዎች በግልፅ እንደሚያስረዱት ይህ የአክራሪነት አዝማሚያ ስር እየሰደደ በመምጣት ለሃገር ደህንነት እና ለህዝብ ሰላም ስጋት ወደ መሆን ደረጃ ደርሷል:: ሁኔታዎች በዚህ አይነት መንገድ የሚቀጥሉ ከሆነ ሃገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ የምትታወቅበት የኃይማኖቶች የመቻቻል ባህል ታሪክ ሆነ ወደመቅረት ደረጃ መውረዱ ሳይታለም የተፈታ ነው:: የሌሎችን ምርጫ እና ነጻነት በመንፈግ እኔ ብቻ የበላይ ልሁን፥ የእኔን እምነት ተቀበሉ በማለት ሕዝብን ማሸበር እና የንጹሓንን ደም ማፍሰስ ለማንኛውም ህሊናው በትክክል ለሚሰራ ሰው ተቀባይነት ያለው ጉዳይ አይደለም::
እንግዲህ እኛ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ለዚህ ከፊታችን ለተጋረጠ ግዙፍ ተግዳሮት ምላሽ መስጠት ያለብን እርሱ በመጣበት የክፋት መንገድ ሳይሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረን እና ምሳሌ በተወልን የፍቅር እና የሰላም መንገድ መሆን ይኖርበታል:: እርስ በእርሳችን መከፋፈል ትተን በፍቅር ህብረታችንን ማፅናት፥ ለሃገራችን ደህንነት እና በእስልምና የአክራሪነት ጭለማ ውስጥ ላሉ ወገኖቻችን መጸለይ እንዲሁም ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ የሆነውን የክርስቶስን የማዳኑን ወንጌል ማወጅ ኃላፊነታችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም::
የክርስቶስ ትምህርት የሚጠሉንንና የሚያሳድዱንን መጥላትና ማሳደድ ሳይሆን ፍጹም በሆነ ፍቅር መውደድ መሆኑን በመገንዘብ ለሙስሊም ወገኖቻቸን ይህንኑ መልካም የሆነውን የክርስቶስ ኢየሱስ ባህርይ ልናሳይ ዘንድ የተገባ ነው:: "ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል:: እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።" የሚለውን የጌታን ቃል ዘወትር በልባችን ልናኖር ይገባናል:: (የማቴዎስ ወንጌል 5:43-45)
ምንጭ:- ኢ.ቴ.ቪ. ሚያዝያ 9/2004
ሪፖርተር ጋዜጣ የሚያዝያ 8/2004 እትም
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ