መጽሐፍ ቅዱስ
M.J Fisher, M.DIV
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
ቁርአን ስለአይሁዶችና ክርስትያኖች ቅዱስ መጽሐፍ የሚናገረውን ችላ በማለት በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስን እንደተሳሳተ በመቁጠርና በመናገር አንቀበለውም ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እራሱ ቁርአን መጽሐፍ ቅዱስን በጣም ብዙ ጊዜ መልካምን ነገር ሲናገርለት ይታያል፡፡ ይህም የተደረገው ቁርአን የራሱን ተቀባይነት እንዲያረጋግጥና እንዲያገኝ ለማድረግ ለበጎ ታቅዶ ነበር፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሰባ አንድ የጥቅሶች ስብስቦች እንደሚታየው መሐመድ ይህንን ያደረገው ልክ እንደ አብርሃም፣ እንደሙሴ እንደ ዳዊት እና እንደሌሎቹ ነቢያት እና ሐዋርያት ነቢይ ተደርጎ እንዲቆጠር ለማድረግ ነበር፡፡ ስለዚህም አላህ በመሐመድ ጊዜ የነበሩ አይሁዶችና ክርስትያኖች የተመለከ አምላክ እንደሆንም ይናገራል ማለትም ከክርስቶስ የምድር አገልግሎት 600 ዓመት በኋላ ገደማ ነው፡፡ ቁርአን አይሁዶችና ክርስትያኖች ከመለኮት የመጣ በመሆኑ ያጠኑትን የቅዱስ መጽሐፍን ትክክለኛነት (ዋጋ ያለው መሆኑን) ያረጋግጣል፡፡
የእስላሞች የመጽሐፍ ቅዱስ ነቀፌታ የመነጨውም ክርስትያኖችና አይሁዶች የተሰጣቸውን መጽሐፍ በርዘዋል (ትርጉም አሳስተዋል) የሚል ዓይነት ሐሳብ ካላቸው የቁርአን ጥቅሶች ላይ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ እራሱን የቻለ ሌላ ምዕራፍ ይኖረናል፡፡ በዚያ በምንመለከተው ምዕራፍ ውስጥ ቁርአን እንዳስቀመጠው ከሆነ ችግሮቹን ለሁለት ይመድባቸዋል፡፡ እነሱም ጣዖትን የሚያመልኩ የነበሩና የራሳቸውን ግጥም የጻፉ እና በክርስትያኖችና በአይሁድ መካከል የነበሩ የሐሰት አስተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን አሳስተው በመተርጎም ለገንዘብ ሲሉ የሐሰት ጥቅሶችን የሸጡ ናቸው ይላል፡፡ እዚህ ጋ መነሳት ያለበት ጥያቄ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጦ ከሆነ የተለወጠው መቼ ነው የሚለው ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ እግዚአብሔር ለምን ቃሉ እንዲለወጥ ፈቀደ የሚሉት ናቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ከመሐመድ በፊት ነው የተቀየረው የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት ሙስሊሞች አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል ምክንያቱም በቁርአን ያሉት ጥቅሶች በመሐመድ ጊዜ በአይሁድና በክርስትያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ይጠና እንደነበረ ይናገራልና፡፡ እንዲሁም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ከመሐመድ በኋላ ነው የተቀየረው የሚለውን ሊቀበሉት አይችሉም ምክንያቱም ዘመናዊው ሳይንስ ይህንን እንዳይናገሩት ያደርጋልና፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት ጥንት በምኩራብና በዓለም ውስጥ ሁሉ ባሉት ቤተክርስትያናት ይጠኑ ከነበሩት ለዘመናት ሁሉ በምንም መልኩ እንዳልተቀየረ የሚያረጋግጡ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ማስረጃዎች አሉ፡፡
አንዳንድ ሙስሊሞችም ይህንን ችግር ለማቃለል ሲሉ የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሚቀበሉና የትኛውን እንደማይቀበሉ (ወይንም የእግዚአብሔር ቃል ነው አይደለም) ለማለት ይሞክራሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት አንዳንድ የቁርአን ጥቅሶች የቶራንን ወይንም ሕጉን ብቻ ከብሉይ ኪዳን ስለሚጠቅሱ ነው (የሙሴን አምስቱን መጽሐፍት) ሌሎች ጥቅሶች ደግሞ መዝሙርን (ዛቡርን) ይጨምራሉ የዳዊትን መዝሙር ዓይነት ጽሑፎች፡ እንዲሁም ደግሞ ወንጌልን (ኢንጅል) የሚሉትን፡፡ እነሱም ቁርአን ‹መጽሐፉን እንደሚቀበል አያስተውሉም› መጽሐፉ ማለት ደግሞ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ስለዚህም መሐመድ በቃሉ ያስታውሳቸው የነበሩት ቃላት የመጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ ክፍል እንደሚደግፉ ያስረዳል (ወይንም ጠንካራ ማስረጃ ነው)፡፡ እንዲሁም ደግሞ በቁርአን ውስጥ ያልተጠቀሱ እጅግ ብዙ ነቢያትና ሐዋርያት መኖራቸውን ሙስሊሞች አያስተውሉም፡፡ ወንጌልን በተመለከተም ደግሞ ቤተክርስትያን አጠቃላይ አዲስ ኪዳንን የክርስቶስ ወንጌል አድርጋ መጥቀሷ እንደሆነ አያስተውሉም፡፡ አሁንም እንደገና ማስታወስ የምንፈልገው ቁርአን መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል የሚደግፍ ሲሆን ነገር ግን ይዘቱንና አስተምሮውን እንደማይቀበል ነው፡፡ ይህንን ነው ሙስሊሞች ማየት ያልቻሉትና ችግር የሆነባቸው፡፡
አንድ በአንድ ነጥቦቹ ከጥቅሶቹ ጋር፡፡
ለቁርአን ድጋፍ የሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል፡- ፍርድን አስመልክቶ የተጻፉት ጽሑፎች በቀደሙት ቅዱሳን መጽሐፍት ውስጥ ማለትም በአብርሃምና በሙሴ መጽሐፍት ውስጥ ይገኛሉ 87.17-19፡፡ የማያምኑት ሰዎች በሙሴና በአብርሃም መጽሐፍት ውስጥ የተሰበኩትን ስብከቶች በፍፁም አልሰሙአቸውምን? 53.36-37፡፡ በአንድ አምላክ ማመን በቁርአንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትምህርት የተሰጠበት እውነት ነው፡፡ የማያምኑቱ ለሙስሊሞች አንዳች ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ከሆነ ተጠይቀዋል፡፡ 21.24፡፡
የነቢያት ባህርይ፡- ነቢያቶች የአዳም፣ የኖህ፣ የአብርሃም፣ እና የእስማኤል ልጆች (ዘሮች)፣ መገለጥን ሲቀበሉ በእንባ በመውደቅ (በእንባ በመሞላት) አምልኮን ሰጥተዋል 19.58፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት እያንዳንዳቸው ፃድቃን ነበሩ 6.83-85፡፡
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስምምነት፡- በቁርአን ውስጥ ያሉት ታሪኮች የተፈጠሩ ተረቶች ሳይሆኑ እርግጠኞችና መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን የሚያረጋግጡ ናቸው 12.111፡፡
ሙሉ ለሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን ይገልጣል፡- ቁርአን ከአላህ ነው ለዚህም ነው ከእሱ በፊት መጥቶ የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ ለሙሉ የሚገልጠው 10.37፡፡
ተጠራጣሪዎች ወደ አይሁዶችና ወደ ክርስትያኖች ተመርተዋል፡- ‹አንተ መሐመድ የቁርአንን እውነተኝነት የምትጠራጠር ከሆነ ከአንተ ሕይወት በፊት የተገለጠውን መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡትን እነዚያን መጠየቅ ይኖርብሃል› 10.94፡፡ ሐዋርያትና ነቢያት በሙሉ ከመሐመድ በፊት መጥተው የነበሩት እሱ ተራ ሰው እንደሆነ እነሱም ተራ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይህንን በተመለከተ ጥርጥር ያለ ከሆነ ሰዎች የመጽሐፉን ሰዎች መጠየቅ ይኖርባቸዋል 21.7፣ 16.43፡፡
ሙሴ፡- ለሰዎች ሁሉ መሪና በረከት ሆኖ ያስተምራቸው ዘንድ ለሙሴ ቅዱስ መጽሐፍ ተሰጥቶት ነበር 28.43፣ 46.12፡፡
ተጠብቋል፡- የአላህን ቃል ማንም ሊለውጠው አይችልም 6.115፡፡
የአይሁድ ሕዝብ እና ቅዱሳን መጽሐፍት፡- የአይሁድ ሕዝብ ሕጉ ወይንም ቶራ (አምስቱ የሙሴ መጽሐፍት) ተሰጥቷቸው ነበር ነገር ግን ለእሱ አልታዘዙም፡፡ እነሱም ልክ እንደ አህያ በከባድ መጽሐፍት ሸክም የከበደባቸው ነበሩ፡፡ እነሱ የተጠሉ ናቸው ምክንያቱም የአላህን መገለጥ አንፈልግም ብለዋልና፡፡ አይሁዶች የአላህ እውነተኛ ብቸኛ ጓደኞች ቢሆኑ ሊሞቱ ይመኙ ነበር ነገር ግን አልተመኙም ምክንያቱም ስህተት የሆነውን ነገር ነውና ያደረጉት 62.5-7፡፡ የእስራኤል ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን፣ ነቢይነትን ተሰጥቷቸው ከሌሎች ሕዝቦች ይልቅ ተመርጠው ነበር፡፡ መጽሐፉ ለእነሱ ከተሰጠ በኋላ ግን እርስ በእርሳቸው ተከፋፈሉ 45.16-17፡፡ ለእስራኤልና ለሙሴ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲወርሱ ምሪት ተሰጥቷቸው ነበር ይህም ለሰዎች መረዳትን እንዲያገኙ መመሪያ ነው 40.53-54፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ማመን ታዟል፡- እነዚያ ለሐዋርያት የተሰጡትን ቅዱሳት መጽሐፍትን የማይቀበሉት በፍርድ ቀን በአንገቶቻቸው ላይ ሰንሰለት ተደርጎባቸው በፈላ ውሃ ውስጥ እየተጎተቱ ወደ እሳት የሚወረወሩት ናቸው 40.69-72፡፡ በአላህ ፈቃድ ብቻ ተዓምራትን ያደርጉ የነበሩ ከመሐመድ በፊት የተላኩ ሐዋርያት ነበሩ፡፡ የእነሱም የአንዳንዶቹ ታሪክ በቁርአን ተተርቷል የአንዳንዶቹም አልተነገረም 40.78፡፡ እውነተኛ አማኞች በቁርአንና በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑት ናቸው 2.4፡፡ ሙስሊሞች በአላህ በቁርአን እንዲሁም ለአብርሃም ለእስማኤል ለይስሐቅ ለያዕቆብ እና ለያዕቆብ ዘር ለሙሴ ለኢየሱስ እና ለሌሎች ነቢያት ለተገለፀው እንደሚያምኑ መናገር አለባቸው 21.36፡፡
ሕዝቦች ሁሉ፡- በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሕዝብ በመካከሉ የኖረና ቅዱስ መጽሐፍ የወረደለት ነቢይ ነበረው 35.23-25፡፡
አንድ ዓይነት እግዚአብሔር፡- ለመጽሐፉ ሰዎች ንገራቸው እናንተ ሙስሊሞች ለእነሱ በተሰጠው በቅዱሳት መጽሐፍት እና በቁርአን እንደምታምኑ ንገራቸው፡፡ የእነሱ እግዚአብሔርና የምታምኑት እናንተ አላህ አንድ ዓይነት እንደሆነ ንገራቸው 29.46፡፡
የዳዊት መዝሙር፡- ለአንዳንድ ነቢያት ከሌሎቹ የበለጠን ትንቢት (መገለጥ) አላህ ሰጣቸው፡፡ መዝሙርም ለዳዊት የተሰጡ ነበሩ 17.55፡፡
ለመሐመድ ድጋፍ፡- አላህ ለሙሴ የመለሰው በጻድቁ ላይ ምህረትን እንደሚያደርግ ነበር እነዚህም በእሱ መገለጥ የሚያምኑት ናቸው እንዲሁም መሐመድን የሚከተሉትን ነው እሱም በፍፁም ያላነበበውና ያልፃፈው ነው (ማንበብና መፃፍ የማይችለው ነው)፡፡ እሱንም ሰዎች ባላቸው በቶራ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ ያገኙታል 7.157፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ተጠንቷል፡- እነዚያ ቅዱሳት መጽሐፍትን የወረሱት ደህና አድርገው አጥንተዋቸዋል፡፡ እናም ስለ አላህ ትክክለኛ ያልሆነን ነገር መናገር አያውቁም፡፡ እነሱም ለመጽሐፍ ቅዱስ እራሳቸውን የሰጡትና በእሱም የሚኖሩት እናም በፀሎት የፀኑት የራሳቸውን ሽልማት ያገኛሉ 7.168-170፡፡ ክርስትያኖችና አይሁዶች አይስማማሙም ነገር ግን የሚያጠኑት አንድ መጽሐፍን ነው 2.113፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚገባ አለመያዝ፡- ስለመጽሐፍ ቅዱስ ምንም ነገርን የማያውቁ ያልተማሩ ሰዎች በክርስትያኖችም በአይሁዶችም መካከል አሉ፡፡ እነሱም ስለመጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቁት ነገር ውሸትንና ግምትን ብቻ ነው፡፡ እነሱም መጽሐፍ ቅዱስን በእጃቸው ይጽፉና በትንሽ ዋጋ ይሸጡታል፡፡ እነሱም ይቀጣሉ 2.78፣79፡፡ አንዳንዶች መጽሐፉን ከበስተኋላቸው ይጥሉታል እንደዚሁም በጣም በትንሽ ዋጋ ይሸጡታል 3.187፡፡ ሌሎች ክርስትያኖችና አይሁዶች ደግሞ አሉ መገለጥን በትንሽ ዋጋ የማይሸጡ፡፡ እነሱም በአላህ በመጽሐፍ ቅዱስና በቁርአን ያምናሉ 3.199፡፡
ብዙ ነቢያት፡- ብዙ ነቢያት አሉ ኖህን አብርሃምን እስማኤልን ይስሐቅን ያዕቆብን ዘሮቹን ኢየሱስን ኢዮብን ዮናስን አሮንን ሰሎሞንን እና ዳዊት መዝሙር የተሰጠውን ጨምሮ፡፡ እንደዚሁም ስማቸው በቁርአን ላይ ያልተጠቀሱ ሌሎች ነቢያትም አሉ 4.163-165፡፡
ቶራህ ታማኝ መጽሐፍ ነው፡- ቶራህ የአላህን ፍርድ የሚናገር መጽሐፍ ነው፡፡ እሱም የመገለጥ መሪና ብርሃን ነው 5.43፣44፡፡
ወንጌል ታማኝ ነው፡- ኢየሱስ የማርያም ልጅ የመጣው ቀድሞ የተገለጠውን ቶራን በማረጋገጥ ነው፡፡ እሱም ምሪትና ብርሃን ያላትን ወንጌልን ተሰጥቶት ነበር፡፡ እሱም ከቶራ ጋር የሚስማማ ነው እናም ወደ ክፉ ለሚያዘነብሉት መሪና ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ክርስትያኖች ስለዚህም ሊፈረድባቸው የሚገባው በወንጌል ውስጥ አላህ በገለጠው መገለጥ መስረት ነው 5.46፣47፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ነው፡- ነቢያቱ ተመርጠው ተመርተው ነበር፡፡ እነሱም መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ እና ነቢይነት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ በመሐመድ ጊዜ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አንቀበልም ቢሉ ቅዱስ መጽሐፍን ለሚያምኑ ለሌሎች ተላልፎ ይሰጣል 6.87-89፡፡
እውነተኛና ሐሰተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች፡- ከመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች መካከል እጅግ በጣም እምነት የሚጣልባቸው እና ምንም እምነት የማይጣልባቸው ደግሞ አሉ፡፡ ከእነሱም ከፊሎቹ መጽሐፍ ቅዱስን በምላሶቻቸው ያጣምማሉ፡፡ እነሱም ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው ብለው የሚናገሩት ነገር ከመጽሐፍ አይደለም 3.75-78፡፡ የሐሰት አስተማሪዎቹም የሚናገሩት ከቶራ ላይ ለመሆኑ ቶራን አምጥተው እንዲያነቡ መጠየቅ አለባቸው እናም አውነትነቱ መፈተን አለበት፡፡ ከንባቡ በኋላ ደግሞ እነዚያ ስለአላህ ውሸትን የፈጠሩት ፈጥረው የተናገሩት ትልቅ ኃጢአተኞች ናቸው 3.93-94፡፡ ስለ አላህ ውሸትን ፈጥሮ ከሚናገር ሰው ይልቅ እጅግ የከፋ ኃጢአተኛ ማንም የለም፡፡ እሱም ምንም ሳይኖረው መገለጥን እንደተቀበለ ይናገራል፡፡ እሱም ልክ ቅዱስ መጽሐፍን እንደሚጽፍ ወይንም ቃልን ከጌታ የሆነ ቃል እንደተቀበለ ይናገራል፡፡ በሚሞትበት ጊዜ መላእክት ሊቀጡት ይመጣሉ 6.93፡፡
እግዚአብሔርን በግል ስለማወቅ፡- አንድ እግዚአብሔር ብቻ አለ፡፡ ክርስትያኖችና አይሁዶች የራሳቸውን ልጃቸውን እንደሚያውቁ አድርገው ያውቁታል፡፡ ነገር ግን ሌሎች በጣዖት አምልኮ መሠረት ነፍሳቸውን አጥተዋል ስለአላህም ውሸትን በመፍጠር እና ኃጢአታዊ ባህሪና መገለጥን በመካድ 6.20-22::
አልተለወጠም፡- የአላህ ቃላት በእውነትና በፍርድ ፍፁም የሆኑ ናቸው፡፡ ፍፁም ተደርገዋል፡፡ ማንም ሊለውጣቸው አይችልም 6.115፡፡
ለክርስትያኖችና ለአይሁዶች ተስፋ፡- የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች እምነት ቢኖራቸውና ከክፉም ቢጠበቁ ይቅር ይባሉ ነበር፡፡ በቶራህና በወንጌል ላይ የተገለጠውን ቢጠብቁ ኖሮ ይሸለሙ ነበር 5.65፣66፡፡ እነሱም በቶራና በወንጌል ላይ የተጻፈውን የማይከተሉ ከሆነ ምሪትን አያገኙም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቅዱስ ቃላት የመለኮት መገለጦች ናቸው ነገር ግን እነሱን ማንበብ ዓመፀኝነትን አምጥቷል ይህም በእምነት ባልሆኑት ላይ ነው 5.68፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-
ከዚህ በላይ በዝርዝር የሰፈሩት ሰባ አንድ የቁርአን ጥቅሶች ስለመጽሐፍ ቅዱስ የሚናገሩት ነገር አስገራሚ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃልና ሰዎች ሁሉ ሊያነቡትና ሊከተሉት ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ለመሆኑ እራሱ በራሱ የሚያረጋግጥ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው የውስጥ ሕይወት የሚናገርና ነፍስን የሚለውጥ መልእክት ያለው ነው፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን በእውነት ለማምለክ የሚፈልግ እውነተኛ አንባቢን የምንጋብዘው ይህን መጽሐፍ በማግኘት ረጋ ብሎ እንዲያነብ እና ስለ እራሱ ሕይወት እንዲያስብበት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ያነበቡ ሰዎች መንፈሳዊ መረዳትን አግኝተዋል ወደ እውነተኛውና አዳኙ እግዚአብሔርም እምነት መጥተዋል ስለዚህ አግኙና አንቡት ትጠቀማላችሁ፡፡ እግዚአብሔርም በቸርነቱ በመንፈሱና በፀጋው ይርዳችሁ፡፡ አሜን፡፡
የትርጉም ምንጭ: The Holy Bible, Chapter 18 of "A Topical Study of the Qur'an From a Christian Perspective" by M.J Fisher, M.Div
ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ: ርእሳዊ የቁርአን ጥናት በክርስትና አይን ሲመረመር
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ