ቁርአን ስለ አቶሞች ይናገራልን?
በJochen Katz
ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ
እንደሚከተለው ያሉ አረፍተ ነገሮችን የምናነብባቸው አንዳንድ የቁርአን ትርጉሞች አሉ፡
“አላህ የብናኝን ክብደት ያህል አይበድልም መልካም ሥራ ብትሆንም ይደራርብባታል ከርሱም ዘንድ ታላቅን ምንዳ ይሰጣል” ቁርአን 4.40
“(ሙሐመድ ሆይ!) በማንኛውም ነገር ላይ አትኾንም ከርሱም ከቁርአንም አታነብም ማንኛውንም ሥራ (አንተም ሰዎቹም) አትሠሩም በገባችሁበት ጊዜ በናንተ ላይ ተጠባባቂዎች ብንኾን እንጂ በምድርም ኾነ በሰማይ የብናኝ ክብደት ያክል ከጌታህ (ዕውቀት) አይርቅም ከዚያም ያነሰ የተልለቀም የለም በግልጹ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈ ቢኾን እንጂ” ቁርአን 10.61
“እነዚያ የካዱትም ሰዓቲቱ አትመጣብንም አሉ በላቸው፡ አይደለም ሩቁን ሁሉ ዐዋቂ በኾነው ጌታዬ እምላለሁ በእርግጥ ትመጣባችኋለች የብናኝ ክብደት ያክል እንኳን በሰማያትና በምድር ውስጥ ከርሱ አይርቅም ከዚህ ያነሰም ኾነ የበለጠ የለም በግልጹ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበ ቢኾን እንጂ” ቁርአን 34.3
በተለይም በቁርአን 10.61 እና 34.3 ላይ በመመስረት ሐሩን ያህያና ሌሎችም ብዙ የሙስሊም ሚሽነሪዎች ቁርአን “የ-ሰብ-አቶሚክ” ነገሮችን መኖር ገልጧል እስከማለት ድረስ መጥተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሌሎች የቁርአን ትርጉሞች እነዚህን ሰብ አቶሚክ ፖርቲክልስ የተባሉትን በተለየ መንገድ አቅርበዋቸዋል፡
የፒክታል ትርጉም “እነሆ! አላህ አይበድልም የጉንዳንን ክብደት ያህል እንኳን እርሱ እጥፍ ያደርገዋል እናም (ለሰራተኛው) ይሰጠዋል ከእርሱም መኖር ታላቅ ሽልማትን ይሰጠዋል” ቁርአን 4.40፡፡
በቁርአን 4.40 ላይ የአርበሪ ትርጉም ደግሞ “እግዚአብሔር የጉንዳንን ክብደት ያህል አይበድልም” ሲል የሂላሊ እና የካን ትርጉም ደግሞ “የአቶም (ወይንም የትንሽ ጉንዳን) ክብደት ያህል አይበድልም” በማለት ያስቀምጡታል፡፡
በቁርአን 10.61ን አርበሪ ትርጉም ላይ ደግሞ የሚከተለውን እናገኛለን “የጉንዳን ክብደት”፡፡ በቁርአን 34.3 ላይ ደግሞ የሳሌ ትርጉም “የጉንዳን ክብደት” በማለት ያስቀምጠዋል፡፡
ምንድነው እየሆነ ያለው? ቁርአን እየተናገረ ያለው ስለ አቶሞች ነው ወይንስ ስለ ጉንዳኖች ነው?
በቁርአን ውስጥ ከዚህ በላይ ያለውን አባባል በተመለከተ የሚናገሩ ስድስት ጥቅሶች አሉ እነርሱም ቁርአን 4.40፤ 10.61፣ 34.3፤22፤ 99.7እና 8 ናቸው፡፡ በእነርሱም ውስጥ ያለው የአረብኛ ቃል “ሚትካላ ታራቲን” የሚል ነው፡፡
እስከ አሁን ድረስ በጣም ጥሩና አጠቃላይ የሆነ የአረብኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት የሚባለው Edward Lane’s Arabic-English Lexicon በ1863-93 የታተመው ነው፡፡ መዝገበ ቃላቱም tharrah ለሚለው ቃል ከሰጣቸው የተዘረዘሩ ትርጉሞች ውስጥ ዋናው የቃሉ ትርጉም የሚለው ትንሽ እና (ገና የተፈለፈለ) ጉንዳን የሚል ነው፡፡
ከተሰጡት የተለያዩ ጥቅሶች ላይ በመመስረት ይህ ቃል ምሳሌያዊ ሆኖ እናገኘዋለን፣ ይህም በጣም ትንሽ የሆነውን ነገር፤ ብናኝ አቧራን ወይንም በጣም ትንሽ የሆነን የወርቅን ብናኝ ለማሳየት ነው፡፡ ይሁን እንጂ “አቶም” የሚለው ቃል በዝርዝር መዝገበ ቃላቱ ውስጥ በጭራሽ የለም፡፡ ይህ እንዲህ ሆኖ እያለ “አቶም” የሚለው ቃል በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ትርጉሞች ውስጥ እንዴት ተገኘ?
አረቦች የግሪክን ጽሑፎች መትርጎም በነበረባቸው ወቅት በቁስ አካል (ማተር) ስነ አሰራር ፅንሰ ሐሳብ ላይ፣ “አቶሞስ” የሚለውን የግሪክ ቃል አግኝተዋል፣ ከዚያም በምን የአረብኛ ቃል ማስቀመጥ እንደሚችሉ ችግር አጋጥሟቸው ነበር፡፡ ስለዚህም የአረብ ፈላስፋዎች ተጠቅመውበት የነበረው ቃል “አል ጎሃር ኦልፋርድ” የሚለውን ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ነጠላ ነገር” ማለት ሲሆን ቃሉም የግሪኩን ስሜት ደህና አድርጎ አስተላልፎት ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በዘመናዊው ጊዜ (ሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲጀመር አካባቢ) “አቶም” የሚለው ቃል ወደ አረብኛው “ታራህ” መተርጎም ጀመረ፣ ይህም ለተራ ሰዎች በሚጻፉ ጽሑፎች እና ለሃይማኖት ሰዎች በሚጻፉ ጽሑፎች ውስጥ ነበር፡፡ ስለዚህም “ታራህ” ይህንን አዲስ ተጨማሪ ትርጉም አገኘ፣ ነገር ግን ይህ ትርጉም በንፅፅር ሲታይ በጣም በቅርብ ጊዜ የተፈጠረ ነው፡፡ በቁርአን ውስጥ ይሁን እንጂ እንዲሁም በሌሎች የአረብኛ ጥሩ ጽሑፎች ውስጥ “ታራህ” የሚለው ቃል በጭራሽ ያንን ትርጉም ይዞ አይገኝም፡፡
በእነዚህ ዘመናዊ የቁርአን የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ውስጥ ምንድነው የሆነው ነገር ብለን ብንል የምናገኘው መልስ በታዋቂ ጽሑፎች ውስጥ፣ “አቶም” በመጀመሪያ እንደ “ታራህ” ሆኖ መተርጎም ጀመረ ከዚያም በኋላ “ታራህ” የሚለው ቃል በቁርአን ውስጥ ገባ (ይህም ይህ ቃል ይህንን አዲስ ትርጉም ከማግኘቱ በፊት በዋናዎቹ ጽሑፎች ውስጥ ተደረገ)፡፡ ቀጥሎም “አቶም” ተብሎ በቁርአን ዘመናዊ ትርጉሞችም ውስጥ ሳይቀር ተተርጉሞ ተቀመጠ፣ ነገር ግን ያ ጊዜውን የሳተ ትርጉም ነው፣ ማለትም ለመጀመሪያዎቹ አንባቢዎች ያልታወቀውን ነገር ከክፍሉ ውስጥ ማንበብ ነው፡፡
“ከአቶም ፅንሰ ሐሳብ ጋር በጣም የተዛመዱ የሆኑትን ጥንታዊ የአረብ ተርጓሚዎች ብትመለከቱ “ታራህ” የሚለውን ቃል ለአቶም በፍፁም አልተጠቀሙበትም፡፡ የግሪክን ስራዎች ወደ አረብኛ ትርጉም በተደረገበትም ጊዜ እንኳን የአረብኛውን “ታራህ” የሚለውን ቃል “ለአቶም” በፍፁም አልተጠቀሙበትም”፡፡
ሙስሊሞች ቁርአን ስለ አቶሞች ያውቃል በማለት ከፀኑ፣ ማድረግ የሚገባቸው ነገር ጥንታዊ የአረብኛ ክፍሎችን መፈለግ ነው፣ ይህ ቃል “አቶም” ተብሎ የተጠቀሰበትን ለማስረዳት ማለትም የቁስ አካል ስነ ስራዎች የተብራሩባቸውን ወይንም የተገለጡባቸውን ጽሑፎች ማግኘት ይኖርባቸዋል፣ ለምሳሌም ያህል ወደ አረብኛ የተተረጎሙ እና ስለ”አቶም” የሚናገሩት የግሪክ ታዋቂ ጽሑፎችን ማግኘት አለባቸው ማለት ነው፡፡
ከዚህም በላይ ታዋቂዎቹ የቁርአን ተንታኞች (የታባሪ ታፍሲር፣ የቆርጣቢ ወ.ዘ.ተ.) ያንን ቃል እንደዚያ በማለት በፍፁም አልተረጎሙትም ይህም የግሪክ “የአቶም” ፅንሰ ሐሳብ በዚያን ጊዜ የታወቀ ቢሆንም እንኳን ጭምር ነው፡፡
አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፡-
ቁርአን 10.61 አልታባሪ (ሚትካላ ታራቲን) ማለት የትንሽ ጉንዳን ክብደት ... ታራህ በነጠላ ለ”ታር”፡፡ እናም “ታር” ትናንሽ ጉንዳኖች ናቸው፡፡ የአረብኛ ምንጭ፡፡
እንዲሁም ቁርአን 4.40፡፡
አል-ቁርጣቢ
የቁርአኑን ትርጉም ከሰጠ በኋላ የሚከተለውን አስቀምጧል፡ ታራህ ማለት ቀይ ጉንዳን ነው እናም በኢብን አባስ እና በሌሎችም መሰረት እርሱ ከጉንዳኖች ሁሉ በጣም ትንሹ ነው፡፡ እንዲያውም ኢብን አባስ የተናገረው እርሱ የጉንዳን እራስ ነው በማለት ነው፡፡
አል-ባይዳዊ
ታህራህን ያስቀመጠው በጣም ትንሽ ጉንዳን በማለት ነው፡፡
አል-ጃላላይን
ታራቲን ማለት በጣም ትንሽ ጉንዳን ነው፡፡
አዝ-ዛማክሻሪ፡
(የታራቲን ክብደት) በጣም የትንሽ ጉንዳን ክብደት ማለት ነው፡፡
ከዚህ በላይ ያሉት ትንታኔዎች በሙሉ (በሙቲአ አል-ፋዲ ከአረቢኛው የድረ-ገፅ ህትመቶች በቀጥታ የተተረጎሙ ናቸው) እነርሱም በወጥነት ታራህን የጠቀሱት እንደ ትንሽ ጉንዳን ወይንም በጣም ትንሽ ጉንዳን አድርገው ነው፡፡
ወደ መጀመሪያው ጥያቄ ለመምጣት፡ ቁርአን “ማቲካላ ታራቲን” የሚለውን አባባል ስድስት ጊዜ ተጠቅሞበታል፡፡ በታዋቂ የቁርአን ተንታኞች አማካኝነት ማቲካላ ታራቲን “የጉንዳን ክብደት” ማለት ነው፡፡ ስለዚህም እርሱ በአረብኛ የምሳሌያዊ አገላለጥ ነው የሚገልጠውም በጣም ትንሽ የሆነ ነገርን ብቻ ነው፡፡ (ትንሽ ነገርን ለመግለፅ የሚያገለግል የአረቢያዊ ዘይቤያዊ ወይንም ምሳሌያዊ አባባል ብቻ ነው)፡፡
ይህ በአረቦች የየዕለት ሕይወት ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኝ በጣም ትንሹ ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጉንዳን ለሁለት ሊከፈል ይችላል፣ ስለዚህም ከዚያም ያነሱ ነገሮች ይኖራሉ (ስለዚህም ቁርአን ከዚያም በታች ስላነሰ ነገር ለመናገር ምንም ችግር አይኖርበትም ማለት ነው)፣ ነገር ግን ጉንዳን አሁንም ምሳሌያዊው “በጣም ትንሽ ነገር ነው” ወይንም “በጣም ትንሽ ክብደት” ያለው ነገር ነው፡፡
ስለዚህም ለእርሱ እኩል የሚሆንን ነገር የምንፈልግ ከሆነ፣ ከዚያም “ማቲካላ ታራቲን” የሚለውን ቃል “የአቶም ክብደት” በማለት በዘመናዊው ቋንቋ መተርጎም የሚያስኬድ ነው በማለት መናገር እንችል ይሆናል፣ ምክንያቱም ለእኛ በአሁኑ ጊዜ “አቶም” በጣም ትንሹ ነገር ነው ይባላልና (ወይንም ደግሞ ቢያንስ እንደዚያ ተብሎ ይወሰድ ነበርና)፡፡ በፍልቅ ትርጉም (በቃሉ ስሜት እንተርጉመው ካልን) ስሜት ይህ ተቀባይነት ያለው ትርጉም ነው ሊባል ይቻላል፣ በሳይንሳዊ ስሜቱ ግን በፍፁም ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም ለመጀመሪያዎቹ አንባቢዎች ወይንም ተቀባዮች በቴክኒካዊ ስሜት ወይንም በሳይንሳዊ ስሜት ቃሉ “አቶም” አይልም ነበርና፡፡ እዚህ ላይ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ቁርአን ሳይንሳዊ አረፍተ ነገርን እየሰጠ አይደለም፤ ነገር ግን እየሰጠን ያለው ሃይማኖታዊ አረፍተ ነገሮችን፤ ወይንም ቲዎሎጂካል አረፍተ ነገርን ነው፡፡ ማለትም እግዚአብሔር “ብናኝም” እንኳን የሆነን የፍትህ ስህተት አይሰራም እያለን ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ጸሐፊው ለማስረዳት ምሳሌያዊ መግለጫን ማለትም “ብናኝ” ወይንም “በጣም ትንሽ” በማለት በምሳሌያዊው ቃል ማለትም “ትንሽ ጉንዳን” ተጠቅሟል፡፡
እንደገናም ደግሞ እንደ ሐሳብ ለሐሳብ ትርጉም ዓይነት ሃይማኖታዊ መልእክት “አቶም” የሚለው ትርጉም ተቀባይነት አለው፤ ነገር ግን ቁርአን በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ስለ አቶም ነው የሚያወራው ወይንም ስለ “የአቶም ክፍልፋዮች” ነው ብሎ መናገር የተሳሳተ ትርጉምና በቁርአኑም ክፍል ላይ በደልን መፈፀም ይሆናል፡፡
በእርግጥ ቃሉን እንደ “አቶም” መተርጎም እንዲሁም ያንን ትርጉም በምሳሌያዊነት መግለጫነቱ ከመውሰድ ውጭ በጥሬው ትርጉም መውሰድ የሚሰጠው ውጤት የሳይንሳዊ ባዶነትን ብቻ ነው፡፡ እስኪ የሚከተለውን ጥቅስ እንመርምረው፡
ተናገር (ኦ መሐመድ ተመልከት ወደ እነዚያ የብዙ ጣዖታት አምላኪዎች እና ፓጋኖች ወ.ዘ.ተ) “እነዚያን ከአላህ ሌላ አማልክት ብላችሁ) የምታስቧቸውን ጥሩ በሰማያትም በምድርም ውስጥ የብናኝ ክብደት ((ወይንም የትንሽ ጉንዳን) የአልሂላ እና የካን ትርጉም የጨመረው) ያክል ምንንም አይችሉም ለነርሱም በሁለቱም ውስጥ ምንም ሽርክና የላቸውም ከነርሱም ለርሱ ምንም አጋዥ የለውም በላቸው፡፡” ቁርአን 34.22፡፡
(ከላይ በተጠቀሱት ሁለት የቁርአን ትርጉሞች ውስጥ እንደተቀመጠው ከሆነ “... የብናኝ ክብደት (ወይንም የትንሽ ጉንዳን) ያክል ምንንም አይችሉም የሚለው የአማርኛው ቁርአን ትርጉም ጋር አይመሳሰሉም የእነርሱ ትርጉም የሚለው (እነርሱም የአቶምን (በአማርኛው ብናኝ) ወይንም የትንሽ ጉንዳንድን ክብደት አይኖራቸውም ወይንም ሊይዙ አይችሉም ነው)፡፡
ይህ ያልተለመደ አቀራረብ አይሆንምን? አንድ ሰው እራሱን ነገሩን ሳያገኘው የማንኛውንም ነገር ክብደት ማግኘት ይችላልን? ስለዚህም ክፍሉ ቃል በቃል ሲወሰድ ይህ አቀራረብ ትርጉመ ቢስ ይሆናል፡፡ በእስልምና ሕግም እንኳን አንድ ሰው የአንድን ነገር ባህርይ ወይንም የተሰራበት ነገር (ተፈጥሮ) ሊኖረው አይችልም፡፡ ኡማር የአብደላን ግመል ክብደት ሊኖረው አይችልም፣ እንዲሁም አሊ የኡትማን ቤት ከፍታ ሊኖረው አይችልም፣ እንዲሁም ዘይነባ የአይሻን ጃኬት ቀለም ሊኖራት አይችልም እንዲሁም ፋጡማ ደግሞ የከዲጃ ማር ጥፍጥና ሊኖራት አይችልም፡፡
ስለዚህም ጽሑፉ ማለት የነበረበት፡
“... እነርሱ አቶምም “ብናኝም” እንኳን የላቸውም (ወይንም ትንሽ ጉንዳን) በሰማይም ወይንም በምድርም ወይንም በማናቸውም ቦታ ምንም ድርሻ እነርሱ የላቸውም. ...” ነገር ግን “ክብደት” የሚለውን መጨመር አረፍተ ነገሩን ወደ ትርጉመ ቢስነት ይቀይረዋል፡፡
የአንድ ነገር ክብደት ተጨባጭ የሆነ የአንድ የተፈጠረ ነገር እውነታ ነው፡፡ እነዚህ ባህርያት ወይንም ነገሮች በሌላ በማናቸው ነገርም ሆነ ሰው ሊወሰዱ አይችሉም እነርሱ ለእራሳቸው ለነገሮቹ የተሰጡ ናቸውና፡፡
ለዚህም አቀራረብ ሊኖር የሚችለው አንድና ብቸኛው ብያኔ “ሚታካላ ታራቲን”፤ የሚለው ውሱን የምሳሌያዊ አገላለጥ ነው እርሱም የሚያመለክተው “በጣም አናሳ ወይንም በጣም ትንሽ የሆነውን ነገር ነው” ይህም በተለይም ምንንም ሌላ ነገር ሳያመለክት ነው፡፡
ምሳሌያዊ አነጋገሮች ሎጂካል መሆን አይኖባቸውም፡፡ በብዙ ቋንቋዎች ውስጥ በጣም ያልተለመዱ ዓይነቶች የምሳሌያዊ አነጋገሮች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ይህ የአረብኛ ቋንቋ ዝም ብሎ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው ካልን፤ ይህንን ሳይንሳዊ ተዓምር አለው ብሎ መውሰድ ቀርቶ፤ እንደ ሳይንሳዊ ትርጉም እንዳንወስደው ሙሉ ለሙሉ ያግደናል፡፡
በሌሎቹ አምስት ጥቅሶች ውስጥ ማለትም በቁርአን 4.40፣ 10.61 34.3 99.7እና 8 ውስጥ፣ የብናኝ ክብደት) “ሚታካላ ታራቲን” = ይሆናል = “የአቶም ወይንም የጉንዳን ክብደት ትርጉም ይሰጣል፡፡ እነዚያ ጥቅሶች ሙሉ ለሙሉ ምሳሌያዊ በመሆናቸው የእግዚአብሔር ፍትሕ ከተወሰነ ነገር ክብደት ጋር በማነፃፀር ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን በዚያ በስድስተኛው ማገናዘቢያ ውስጥ ማለትም በቁርአን 34.22 ላይ አቀራረቡ ቃል በቃል ሲወሰድ ምንም ትርጉምን አይሰጥም፣ ትርጉም ሊሰጥ የሚችለው በምሳሌነት ሲወሰድ ብቻ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ “ታራን” እንደ “አቶም” ለምን እንደተተረጎመና ይህ ጥቅስ ሳይንሳዊ መረጃ በመስጠት ሳይንሳዊ ተዓምር አለው ማለት ችግር የሚያስከትል ለመሆኑ ሌላ ሁለተኛ ምክንያትም ይገኛል፡፡ የሚከተለውን እንመልከት፡-
“የአቶም” ክብደት ምንድነው?
በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ሙስሊሞች ሳይንስን ለማግኘት ከፈለጉ እነርሱ ለዚህ አቀራረብ ሳይንሳዊ ትክክለኛነትን መጠቀም ይኖባቸዋል፡፡ የቁርአን ጸሐፊ እጅግ በጣም ብዙ የተለያየ የክብደት መጠን ያላቸው የተለያዩ አቶሞች መኖራቸውን የሚያውቅ አይመስልም! (ይህንን ለማየት የኬሚስትሪ የፔሬዲክ ቴብልን መመልከት በጣም ጠቃሚ ነው) ለምሳሌም ሎረንቲየም የተባለው አንድ አቶም ሃይድሮጅን ከተባለው አቶም 260 ጊዜ ይከብዳል፡፡ ስለዚህም ስለ አቶም ክብደት ስንናገር ምን ማለታችን ነው?
እኛ የምንናገረው ስለ አንድ ዓይነት የጉንዳን ዝርያ ከሆነ እነርሱ ቢያንስም ቢበዛም ተቀራራቢ የሆነ ክብደት ይኖራቸዋል በተለይም በዕድሜያቸው በጣም ገና የሆኑትና ወይንም አዲስ የተፈለፈሉት፡፡ አንድ ጉንዳን ቀጠን ያለ ሌላው ደግሞ ወፈር ያሉ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል ይሁን እንጂ እነርሱ በጣም ተቀራራቢ ነው የሚሆኑት፡፡ ስለዚህም ስለ ጉንዳኖች ክብደት መነጋገር አሁንም ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በሳይንሳዊ መልኩ ስለ አቶም ክብደት ማውራት ስለ የትኛው አቶም እንደምንናገር በትክክል ካልተናገርንና ካልወሰንን በስተቀር በጭራሽ ምንም ትርጉም የማይሰጥ ይሆናል፡፡
በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ሳይንሳዊ አረፍተ ነገርን ለመፈለግ መሞከር እነርሱ የተጻፉበትን አላማ ሙሉ ለሙሉ ያጠፋዋል፡፡ ከቁርአን 34.22 በስተቀር ይህንን አገላለጥ ለተጠቀሙት ጥቅሶች (ማለትም 4.40፣ 10.61፣ 34.3፣ 99.7ና8) ጥቅሶቹ ያሉበት ዓውዱ የመጨረሻው ዳኛ ነው፤ ስለዚህም ሐሳቡ የእግዚአብሔር ፍርድ ሁሉን ነገር ሊበይን ይችላል የሚል ሲሆን፤ እርሱም ትንሹን ጥፋት የሚቀጣና ትንሹንም መልካም ነገር የሚሸልም ነው (በሰዎች የተደረጉትን)፡፡
እነዚህ ጥቅሶች የሚያብራሩት በጣም ትንሽ ከሆነ ክብደት ጋር በማወዳደር የሚያሳዩት የእግዚአብሔር ፍርድ ምን ያህል በጣም ሁሉን (ዝርዝር ነገርን ወይንም ምንም የሚያመልጠው ነገር አለመኖሩን) ነገር የሚያካትት መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ይህም የጉንዳንም ክብደት ይሁን የአቶም ክብደት ነው እርሱም ምሳሌያዊ አነጋገር ነው ምክንያቱም ድርጊቶች እንደ ቁሳ-አካላዊ ነገሮች ሊመዘኑ ስለማይችሉ ማለት ነው ምንም ትንሽ ይሁኑ እንኳን፡፡ ስለዚህም እነዚህ ጥቅሶች ቃል በቃል ሊወሰዱ አይችሉም፤ ከወሰድናቸው ግን ችግር ውስጥ እንገባለን ማለት ነው፡፡ እነዚህን ጥቅሶች የምር አድርገን ስንወስድ የሚሆነው መሰረታዊ ነገር ሃይማኖታዊ መልእክት ብቻ እንዳላቸው ነው፤ ነገር ግን ሳይንሳዊ መልእክት በምንም መልኩ በእርግጥ ሊኖራቸው አይችልም፡፡
አቡ አላ ሞዱዲ በጣም የተከበረ የሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሙስሊም ሊቅ ነበር እርሱም የቁርአን ተርጓሚና አብራሪ ነበር፡፡ በጊዜው ከነበሩት ጓደኞቹ በተቃረነ መልኩ “ሚትካላ ታራቲን” ምሳሌያዊ አገላለጥ የነበረ መሆኑንና የቁርአን ጸሐፊ በምሳሌያዊ አነጋገር ይጠቀም እንደነበረ ገልጧል፡፡ እርሱም ይህንን ገለጣ የተረጎመው (ቢያንስ በእነዚህ አንዳንድ ጥቅሶች ውስጥ) እኩያ ያለውን የእንግሊዝኛ ምሳሌያዊ አባባልን በመጠቀም ነበር፡፡
ቁርአን 4.39-42፣ ደህና ምን ጉዳት በእነርሱ ላይ ይመጣባቸዋል፣ በአላህ የሚያምኑ ከሆነ በመጨረሻው ቀን እና አላህ ከሰጣቸው ውጭ ቢያሳልፉስ? እነርሱ ይህንን ካደረጉ አላህ በእርግጥ የእነርሱን ስራ አዋቂ ነው፡፡ በእርግጥ አላህ ማንንም አይበድልም በነጥብም (በቅንጣትም) እንኳን፡ አንድ ሰው መልካምን ቢሰራ እርሱ እጥፍ ያደርገዋል ከዚያም ከእራሱ ብዙ ሽልማትን ይሰጠዋል፡፡
ቁርአን 10.61-65፡ ኦ ነቢዩ፣ የምትሳተፍበትን ማንኛውንም ስራ እና የምታስታውሰውን የቁርአንን ማንኛውንም ክፍል በተመለከተ እኛ እንመሰክራለን፣ እንዲሁም ደግሞ እኛ እናያለን፡፡ ኦ ሰዎች የምታደርጉትን ማንኛውንም ነገር ሁሉ፡ ምክንያቱም የማንኛውም ነገር ቅንጣት፣ ትንሽ ወይንም ትልቅ በምድርና በሰማይ ከእናንተ ጌታ የተደበቀ የለምና እንዲሁም ሁሉም ነገር በግልፅ በመዝገብ ላይ ነው፡፡
ምንም እንኳን ዩሱፍ አሊ “አቶም” የሚለውን ቃል ለመጠቀም ለተነሳው ፈተና እጁን ቢሰጥም በብዙዎቹ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ቁርአን 4.40ን ሲተረጉም ጉዳዩን በጣም በግልጥ አይቶታል፡
“እግዚአብሔር በመጨረሻው ደረጃ ላይ በፍፁም አይበድልም፡ መልካም ነገር ተሰርቶ ከሆነ፣ እርሱ እጥፍ ያደርገዋል እንዲሁም ከእራሱ ሕልውና ታላቅ ሽልማትን ይሰጣል፡፡”
በመጨረሻም የአንድ ረጅም ሐዲት ክፍል ቀጥሎ ይገኛል እርሱም “አቶም” የሚለው አተረጓጎም ያልተለመደ መሆኑን ግልፅ ያደርጋል፡
“... ከዚያም እንደዚህ ይባላል፤ “ኦ! መሐመድ እራስህን አቅናና ተናገር፣ አንተም ትሰማለህና፣ ጠይቅም ትሰጣለህና (የጠየቅኸውን) ማልድ፣ ያንተም ምልጃ ተቀባይነት አለውና” እኔም እንዲህ እላለሁ፤ “ኦ ጌታ ሆይ የኔ ተከታዮች! የኔ ተከታዮች!” ከዚያም እንዲህ ይባላል፤ “ሂድና በልባቸው ውስጥ የአንዲት ገብስ ክብደት እምነት ያላቸውን ሁሉ ከሲዖል ‹እሳት› አውጣቸው” እኔም እሄዳለሁኝ እንደዚሁም አደርጋለሁኝ እርሱንም ለማመስገን እመለሳለሁኝ በተመሳሳይ ምስጋናዎች፣ እንዲሁም በፊቱ ወድቄ እሰግዳለሁኝ፡፡ ከዚያም እንዲህ ይባላል፣ “ኦ መሐመድ እራስህን አቅናና ተናገር አንተም ተሰማለህና እንዲሁም ጠይቅ (የጠየቅኸው) ይሰጥሃልና፣ ማልድ ምልጃህ ተቀባይነት ይኖረዋልና” እኔም እላለሁኝ፣ “ኦ ጌታ የኔ ተከታዮች! የኔ ተከታዮች!” እኔም እባላለሁኝ “ሂድናየትንሽ ጉንዳን ‹ሚታካላ ታራቲን› ያክል ክብደት ወይንም የሰናፍጭ ቅንጣት ክብደት ያክል እምነት በልባቸው ውስጥ ያላቸውን ከዚያ ውስጥ አውጣቸው” እኔም እሄዳለሁ እንደዚሁም አደርጋለሁ ተመልሼም በተመሳሳይ ምስጋና አመሰግነዋለሁ እንዲሁም በፊቱ ወድቄ እሰግዳለሁ፡፡ እንደዚህም ይባላል “ኦ መሐመድ እራስህን አቅናና ተናገር አንተም ትሰማለህና እንዲሁም ጠይቅ ምክንያቱም (የጠየቅከው) ይሰጥሃልና ማልድ ምልጃህም ተቀባይነት ያገኛልና” እኔም እላለሁ፣ “ኦ ጌታ፣ ተከታዮቼ! ተከታዮቼ!” ከዚያም እርሱ እንዲህ ይላል “ሂድና በልባቸው ውስጥ በጣም ቀላል ከሆነችው የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል የቀለለ እምነት ያለባቸውን ሁሉንም ከእሳት ውስጥ አውጣቸው” እኔም እሄዳለሁ እንደዚሁም አደርጋለሁ”” (ሳሂህ አል-ቡካሪ ጥራዝ 9 መጽሐፍ 93 ቁጥር 601)፡፡
ትናንሽ ጉንዳኖችና ቅንጣት ፍሬዎች ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ክብደትን በተመለከተ ይመሳሰላሉ፣ መጠንን በተመለከተ ሁለቱም በተመሳሳይ ዓይነት የመመዘኛ መስፈርት ስርዓት ውስጥ ናቸው፡፡ በሌላው ጎኑ ግን “አቶሞች”ና “ቅንጣት ፍሬዎች” በጭራሽ የማይመሳሰሉ ናቸው፡፡ እነርሱም በጣም የተራራቁ ናቸው ስለዚህም እነርሱን ለአንድ ነገር ማገናዘቢያነት በአንድ ላይ ማምጣት ያልተለመደ ነገር ነው የሚሆነው፡፡ በእርግጥ ይህ ሐዲት የሚያሳየው ከ”ገብስ ቅንጣት” ወደ “ትንሽ ጉንዳን” ከዚያም “በጣም ቀላል በጣም ቀላል የሰናፍጭ ቅንጣት” ያለውን እድገት ነው፡፡ በግልፅ ትንሽ ፍሬዋ የሰናፍጭ ቅንጣት ከትንሽ ጉንዳንድ እንደምታንስ ግንዛቤ ነበር፡፡ ትንሽ የሰናፍጭ ቅንጣት በዚህ ሐዲት ውስጥ የትንሽነት ማወዳደሪያ የመጨረሻው ደረጃ ናት፡፡ ስለዚህም “ትንሽ ጉንዳን” ማለት “አቶም” ማለት እንዳልሆነ በማሳየት፤ የተጻፈው ቃል “ሳይንሳዊ የአቶም ምልክት ነው የሚለውን” ክርክር በእርግጥ የማይቻል ያደርገዋል፡፡ “ትንሽ ጉንዳን” ማለት “አቶም” ነው የሚለው አተረጓጎም በእነዚህ የዓረፍተ ነገሮች እድገት ውስጥ የታቀደውን ትርጉም ያጠፋዋል፡፡
ስሊዘህም የቁርአን ጸሐፊ ያየው የሰናፍጭ ቅንጣት በመጠኑ ከትንሽ ጉንዳን ጋር በክብደት እኩል ልትሆን እንደምትችል ነው ይህ አቀራረብ ደግሞ ከቁርአን 21.47 እና 31.16 ከ ቁርእነ 4.40፣ 10.61. 34.3. 99.7እና 8 ጋር በማወዳደር ሊገኝ ይችላል፡፡ ያለምንም ጥርጥር ቁርአን በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ስለ አቶሞች ምንም አይናገርም፡፡
የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡
ቁርአን ውስጥ ሳይንስ አለ ስለዚህም ቁርአን ከአላህ የመጣ መጽሐፍ መሆን አለበት የሚለው ሐሳብ በአሁኑ ጊዜ እንደ ዋነኛ መከራከሪያ ሆኖ በብዙ ሙስሊሞች ዘንድ ይጠቀሳል፡፡ የቅርብ ዘመን አመጣሽ የሆነው ይህ የመከራከሪያ ሐሳብ በቀደሙት የሙስሊም ሊቃውንት ዘንድ የማይታወቅና አገልግሎት ላይ ያልነበረ ብቻ ሳይሆን የእስልምና እምነትንና የቁርአንንም ታማኝነት የሚገዳድር ነው፡፡ ስነ ዘዴውን የሚጠቀሙ ሙስሊሞች ሁሉ የእምነታቸውን መጽሐፍ ቁርአን፣ እራሳቸውንም ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ጥለዋል፡፡ ይህንንም ለማስረዳት ከሚጠቀሱት የብዙ ሳይንሳዊ ጥቅሶች መካከል ከዚህ በላይ የቀረበው “የአቶሞች ክብደት” ጉዳይ አንዱ ነው፡፡
ቁርአን ስለአቶም ምንም የሚናገረው ነገር እንደሌለ ከዚህ በላይ ያለው ጽሑፍ በሚገባ አሳይቷል፣ ጥያቄው ግን ስለ “አቶም” ምንም ነገር የማይናገሩትን ጥቅሶች በተሳሳተ የአተረጓጎም ዘዴ እንደሚናገሩና ቁርአን ሳይንሳዊ ነው ለማለት ለምን አስፈለገ? ቁርአን የአምላክ ቃል ከሆነ የአምላክ ቃል መሆኑን ለምን እራሱ በራሱ ማስረጃ አይሰጠንም? ለምሳሌ ያህል፡ በታሪክ የተረጋገጠ እውነታዎችን በመያዙ፣ ለነዚህ እውነታዎች የሚጠቀሱ ማስረጃዎችን በማፍራቱ ወ.ዘ.ተ ማንሳት እንችላለን፡፡ የተሳሳተ ትርጉምን በመጠቀምና በመስጠት “ትክክል ያልሆነውን ነገር ትክክል ባልሆነ ነገር”፤ ትክክል ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት ይሳካልን፣ ደግሞስ ይገባልን? የምናምነው ሁሉን የሚያውቀው አምላክ ከሆነ በዚህ አካሄድ ደስተኛ ሆኖ ጥረታችንን ይቀበለዋልን? እንደዚህ ገፅ አዘጋጆች አመለካከት ሰዎች የአምላክን ቃል በተሳሳተ መንገድ ለማረጋገጥ መነሳት የለባቸውም፡፡
ቁርአን ሳይንሳዊ ቃላት አሉትና ሳይንሳዊ፣ ይህም እውነታ የአምላክ ቃል መሆኑን ያረጋግጣል የሚለው አካሄድ በአሁኑ ጊዜ ቁርአንን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ጥሎታል፡፡ ምክንያቱም የተባሉት ቃላትና የቃላቶቹ መገኛ አውድ እንዲሁም በተመሳሳይ የተጠቀሱበት ቦታ ከዚህም ባሻገር እነዚያ ጥቅሶችና ቃላት በመሐመድ መቼ እንደተነገሩ በዝርዝር እንዲጠና ምክንያትንና መንገድን ከፍቷል፡፡ ከዚህም በመቀጠል ቃላቶቹን በመጠቀም ሳይንሳዊ ትንተና ለማድረግ ሰዎች እንዲነሳሱ አድርጓል፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ሐሳቦቹን በጭፍን ከመቀበል ይልቅ የነገሮቹን እውነታነት በይበልጥ እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል፡፡
በውጤቱም በቁርአን ውስጥ ሳይንስ አለ የሚለው ዘመን አመጣሽ ክርክር ለብዙ ሙስሊሞች እንዳልተዋጠላቸው ግልፅ እየሆነ እየመጣ ነው፡፡ ቁርአን ሳይንሳዊ ትንቢት እንዲኖረው፣ የማይሉትን እንዲሉ በትልቅ ጥበብና ልፋት የሚጠመዘዙት ጥቅሶቹና አጠቃላይ አካሄዶች አስገራሚዎች ናቸው፡፡
ከዚህ የተነሳ አዘጋጆቹ ለአንባቢዎች የሚያሳስቡት የሚከተለውን ጥያቄ እንዲጠይቁ ነው፡፡ የማመልከው አምላክ በእርግጥ እውነተኛውና ብቸኛው የሰማይና የምድር ፈጣሪ ነውን? ከሆነ የሕይወቴ መመሪያ የሆነው ቃሉ፣ እንዲህ ዓይነት ምስቅልቅል ነገር ሊኖርበት ይገባልን? ከአሁኑ ጽሑፍና ከሌሎችም እንዳስተዋልኩት ሁሉ እየተከተልኩት ያለው እምነት በእርግጥ ትክክል ሆኖ ባይገኝስ መጨረሻዬ ምንድነው የሚሆነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች አስቡባቸው እናም እግዚአብሔር ወደ እውነቱ እንዲመራችሁ አጥብቃችሁ ፀልዩ፣ በእነዚህ ጥያቄዎቻችን ሁሉ እኛን የረዳንና የመራን ጌታም በፀጋውና በፍቅሩ ይርዳችሁ፣ ይምራችሁም፡ አሜን፡፡
የትርጉም ምንጭ: Does the Qur'an Speak about Atoms?
ለእስልምና መልስ አማርኛ ዋናው ገጽ